ዜና፡ ረሃብ በየ28 ሰከንድ አንድ ሰው ሊገድል ይችላል ተብሎ ተተነበየ፤ በምስራቅ አፍሪካ የምግብ እጦት ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱን ኦክስፋም አስታውቋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2015 ዓ.ም፡- በቀጣይ ሐምሌ ወር በምስራቅ አፍሪካ የምግብ እጦት ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚባባስ እና ረሃብ በየ28 ሰከንድ አንድ ሰው ሊገድል እንደሚችል ኦክስፋም አመላከተ።

የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው ረሃብ፣ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚታየው ግጭት እና የምግብ ዋጋ መናር ከ40 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የቀጠናው ህዝቦችን ለከፍተኛ ረሃብ እንደሚጋለጥ ኦክስፋም ማስጠንቀቁን ቴሌግራፍ ጋዜጣ በድረገጹ አስታውቋል። በረሃብ የሚጠቃው ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጻር የሁለት ሶስተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው 85ሺ የሚሆኑ በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የሚገኙ ሰዎች ለከፋ ረሃብ ደረጃ ጫፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

የሶማሊያ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከፊል አከባቢዎች ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ምንም አይነት ዝናብ አለማግኘታቸውን ያስታወቀው የኦክስፋም በተለይ ደቡብ ሱዳን ለአምስት ተከታታይ ወቅት በጎርፍ በመጠቃቷ የህዝቡን የማምረት አቅም እንደጎዳው ገልጿል።  በሱዳን የተፈጠረው ግጭት በቀጣይ ወራት ከሁለት እስከ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ህዝብ ለምግብ ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችልም ኦክስፋም ግምቱን አስቀምጧል።

በአለም አቀፍ ደረጃ 345 ሚሊየን ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ ለምግብ ችግር መጋለጡን እና 43 ሚሊየን የሚሆነውም ወደ ከፋ ረሃብ ደረጃ እየተጠጋ መሆኑን የእንግሊዙ ቴሌግራፍ ጋዜጣ በድረገጹ አስነብቧል።  

ሰዎች በርሃብ ምክንያት እየሞቱ ያሉት በቂ ምግብ ስለሌለ አልያም በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ሳይሆን በፖለቲካዊ አካሄድ ችግር እና ኢፍትሃዊነት ሳቢያ ነው፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ምንም አይነት አስተዋጽኦ ባላደረጉበት የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ክፉኛ በመጎዳታቸው ለአየር ንብረት ቀውስ መከሰት ዋነኛ ተጠያቂ ከሚሆኑት ሀገራት መካከል የሆኑት የቡድን ሰባት ሀገራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የማገዝ የሞራል ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ማግኑስ ኮርፊክሰን የኦክስፋም የሰብአዊ ረድኤት ሃላፊ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።

ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ የሚያልፉ ቀናት ልናስቀረው የምንችለውን ሞት እንዲጨምር ያደርጋል ያሉት ሃላፊው ከነገ በስቲያ አርብ የቡድን ሰባት ሀገራት ቀጣይ ስብሰባ እለት መሪዎቹ ወደ እራት እስኪያመሩ ድረስ ከ250 ሰው በላይ ይሞታል ሲሉ ሁኔታው የሚያስከትለውን ጉዳት ገልጸዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.