በጎፋ ዞን የመራጮች ምዝገባ ሂደት ፤ ፎቶ- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያከሄደው ሕዝበ ውሣኔ፣ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች በመፈፀሙ የተደረገው ምዝገባ እንዲሠረዝ ማድረጉን አስታወቀ።
ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሳኔ ከታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄደ ባለው የመራጮች የምዝገባ ሂደት ላይ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች ስር በሚገኙ በአስር ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በተፈፀሙ የህግ ጥሰቶች ምክኒያት የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ተደርጓል ብሏል፡፡
እንደ ቦርዱ ገለፃ፣ በዎላይታ ዞን ዱቦ ምርጫ ጣቢያ አቶ መሰለ ኤሊያስ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ የመመዝገብ የህግ ጥሰት ተፈፅሟል፣ በተጨማሪም የቦርዱ ሠራተኛ ላልሆነ አቶ ወልዴ ወራጆ ለተባለ ግለሰብ ቁልፍ በመስጠት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ ማድረግ እንዲሁም በዞኑ ዶላ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ንዑስ ጣቢያ ውስጥ አቶ አርጃ አሊሶ ከሚባል ግለሰብ ስም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ የመመዝገብ የህግ ጥሰቶች ተፈፅመዋል፡፡
ጎፋ ዞን ጃዉላ ጎሬ አዳ ምርጫ ጣቢያም ተመሳሳይ የሆነ ወይንም በአንድ ሰው የተፈረመ በሚመስል ፊርማ ከአንድ በላይ ካርዶችን ወጪ ማድረግ የህግ ጥሰት መፈፀሙን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
በምዝገባ ሂደቱ፣ በአስሩ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በተፈፀመ የህግ ጥሰቶች፣ የጣቢያዎቹ ሠራተኞች ከኃላፊነታቸው እንዲነሡ፣ በተጨማሪም ሁሉም የምርጫ ጣቢያው ሠራተኞች እና ግብር-አበሮቻቸው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው ውሳኔ ማስተላለፉን ምርጫ ቦርድ ትላንት ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በፌስቡከ ገፁ ባወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባውም አዲስ ሠራተኞች ተመልምለው በድጋሚ እንዲደረግ መመሪያ የሰጠ ሲሆን በቀጣይም ምዝገባውን ለማከናወን እና ያለፉትን የምዝገባ ቀናት ለማካካስ የሚያስፈልጉትን ተጨማሪ ቀናት እና ምዝገባው እንደገና የሚጀመርበትን ቀን እንደሚሳውቅ ገልጧል፡፡
የፌደሬሽ ምክር ቤቱ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሚገኙ 6 ዞኖች ማለትም በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዲኦና በጎፋ እንዲሁም በአምስት ልዩ ወረዳዎች ማለትም በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ አሌ፣ በአማሮና በደራሼ ልዩ ወረዳዎች በጋራ ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የመመስረት ጥያቄ በማቅረባቸው ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
ምርጫ ቦርድም በስድስቱ ዞኖች እና በአምስቱ ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያካሄድ አስታውቋል፡፡ ለሚያካሄደውም ህዝበ ውሳኔ ከታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ እያደረገ ይገኛል፡፡
ስድስቱ ዞኖች አና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በመሆን አዲስ ክልል ለመፍጠር በሚያደርጉት ሕዘበ ውሳኔ ላይ በአጠቃላይ 3,106,585 (ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ስድስት ሺ አምስት መቶ ሰማንያ አምስት) ሰዎች በምርጫው ሊሳተፉ እንደሚችሉ ምርጫ ቦርድ ያስታወቀ ሲሆን ህዝበ ዉሳኔዉ የአብላጫ መራጮችን ይሁንታ ካገኘ በኢትዮዽያ 12ኛዉን ክልል ለመመስረት ያስችላል።አስ