አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4/2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመቀለ ከተማ በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ከትላንት በስቲያ የቅድመ ምርጫ ግምገማ መድረክ ማካሄዱ ተገለጸ። በፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ተካፍይ የነበረው የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ ምክክሩ መካሄዱን ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል።
የውይይቱ አላማዎች በትግራይ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የቅድመ ምርጫ ግምገማ ማካሄድ፣ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጁነት መረዳት እና በክልሉ ምርጫውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመለየት ያለመ መሆኑን ዶ/ር ጸጋዘአብ አስታውቀዋል።
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የትግራይ ክልልን ጨምሮ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች በ2016 ዓ.ም ለማካሄድ መታቀዱን ምርጫ ቦርድ ከሁለት ቀናት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የምርጫ ቦርድ የመቀለ ቅርንጫፍ ባልደረባ፣ ቢሮው ስራ መጀመሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች በተመለከተ የተነገራቸው ነገር እንደለሌለም አስታውቀዋል።
የምርጫ ቦርድ የመቀሌ ቅርንጫፍ አስተባባሪዎች በመድረኩ ዙሪያ ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጡ በዋናው ጽ/ቤቱ ሃላፊዎች መከልከላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።
ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት ወቅት በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ፓርቲዎች ሁሉም በሚባል መልኩ የየራሳቸውን ምልከታ ማቅረባቸውን የገለጹት ዶ/ር ጸጋዘአብ ከበርካታ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም የሚል አስተያየት መሰንዘሩን ገልጸዋል። በምክንያትነት ከቀረቡት መካከል የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆን አንዱ መሆኑ የነገሩን ጸጋዘአብ ካህሱ (ዶ/ር) ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጋ የክልሉ ነዋሪ በተፈናቀለበት ሁኔታ እና ምርጫ የሚካሄድባቸው ቦታዎችስ የትኞቹ ናቸው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባላገኘበት ማለትም የትግራይ ክልል ሉአላዊ ግዛት ባልተከበረበት ሁኔታ እንዴት ምርጫ ይደረጋል የሚሉት እንደሚገኙበት አመላክተዋል።አስ