አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10/2015 ዓ.ም፡- መንግስት በቅርቡ በአማራ ክልል ተካሂዶ በነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ያሰራቸውን ሰባት ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ጠየቀ። በእስር ከሚገኙት ጋዜጠኞች መካከል በአንዷ ላይ የተፈጸመው አካላዊ ጥቃት እንዲጣራም ተቋሙ ጠይቋል። አምነስቲ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ የማሰማት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዲያስጠብቅ ጠይቋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት በአማራ ክልል በበርካታ ቦታዎች ከተካሄደው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ሀይል የተቀላቀለበት እና የጥይት ተኩስት የተካተተበት መሆኑ፣ ሁለት የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች መገደላቸው እና በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር ከተሞች የተካሄደው የጅምላ እስር እንዳሳሰበው አመላክቷል።
ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት ሰራተኞች ያለምንም ማስፈራሪያ፣ ትንኮሳ እና ማሸማቀቅ እንዲሰሩ ማስቻል ይገባል ያለው አምነስቲ ይህም ሞያቸውን ይበልጥ እንዲተገብሩ ለማስቻል ወሳኝ መሆኑን አስገንዝቧል።
ገነት አስማማው፣ ጌትነት አራጋው፣ አራጋው ሲሳይ፣ መስከረም አበራ፣ አባይ ዘውዱ፣ ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው ላይ የተፈጸመው እስር በመናገር ነጻነት እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ሲሉ የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ፍላቪያ ምዋንጎቭያ ገልጸዋል። በጋዜጠኞቹ ላይ የተመሰረተው ክስ ውድቅ እንዲደረግ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። በጋዜጠኛ ገነት አስማማው ላይ የተፈጸመው አካላዊ ጥቃት ምርመራ ተደርጎበት ፈጻሚዎቹ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ፍላቪያ ምዋንጎቭያ ገልጸዋል።
ማንኛውም ሰው ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ የማሰማት መብት አለው ያሉት ሃላፊዋ መንግስት ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን የማሰማት መብታቸውን ሊያስጠብቅላቸው ይገባል ብለዋል። በአዲስ አበባ በጅምላ የታሰሩ ሰዎች መብታቸው ተጠብቆ መደበኛ የክስ ሂደት ሊጀመርላቸው እንደሚገባ ካልሆነ ደግሞ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ አሳስበዋል።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ በተመረጡ የማህበራዊ መተግበሪያዎች ላይ በመንግስት የተጣለው ገደብ ሶስተኛ ወሩን እያስቆጠረ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህ ገደብ እንዲነሳ እና መረጃ የማግኘት እና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያስከብር ተቋማቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይጠይቃል ብለዋል።