ዜና፡ መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የነዳጅ ድጎማው ለሌብነት መጋለጡ በጥናት መረጋገጡ ተገለፀ

ፎቶ- ኢዜአ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7/ 2015 ዓ.ም፡- መንግስት ከሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የነዳጅ ድጎማው ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌብነት መጋለጡን በጥናት አረጋግጫለው ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ። አክሎም ኮንትሮባንድና ብክነትም በስፋት እየተስተዋለበት መሆኑን ገልጧል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማው የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ፣ በነዳጅ ላይ የሚስተዋለውን ኮንትሮባንድ ንግድና ብክነትን ለማስወገድ ያለመ ቢሆንም የድጎማው አተገባበር ሰፊ ክፍተቶችና ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በነዳጅ ድጎማው አተገባበርና አፈፃፀም ሂደት ላይ ያደረገው ጥናት ማመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንደገለፁት የነዳጅ ማደያዎችና ችርቻሪዎች አካባቢ ሌብነትና ህገ ወጥነት እንዲሁም የኮንትሮባንድና ብክነት በስፋት የሚስተዋል ነው።

ከዚህም አልፎ ድጎማው ከህብረተሰቡ ይልቅ አሽከርካሪዎች ባልተፈለገ መልኩ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸው ድጎማ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መደበኛ አገልግሎት መስጠት ትተው በኮንትራት ስራ ላይ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው የ90 ብር ታሪፍ እስከ 200 ብር እንዲሁም የ300 ብር ታሪፍ እስከ 600 ብር እያስከፈሉ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ በትራንስፖርት ስምሪት አካባቢ የተቀናጀ ስምሪትና ቁጥጥር ያለመኖር፣ የንግድና የትራንስፖርት ዘርፉን የሚመሩ የስራ ሃላፊዎችና ሙያተኞች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያለመወጣትና ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆን ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሰራር ማጠናከር፣ ድጎማውን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በ’ጂፒ ኤስ’ ቴክኖሎጂ መቆጣጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ዓላማን መሰረት ያደረገ አሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚገባም የተጠቆመ ሲሆን አተገባበሩ ወጥና ውጤታማ እንዲሆን ከፌዴራል ጀምሮ ክልሎች፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ጨምሮ አዋጁን በባለቤትነት መፈጸም እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በየወሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መንግስት ለነዳጅ ያወጣ የነበረውን ወጪ ማዳን መቻሉ ተገልጿል።

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ትግበራው ይፋ በሆነበት ወቅት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ ተቀራራቢ የሊትር መጠን ግምት በጥናት መለየቱን ገልፀው ይህም እያንዳንዱ ተሸከርካሪ የሚጠቀመውን የነዳጅ መጠን ያገናዘበ ስሌት በመቀመጡ ተሽከርካሪዎቹ “ያለ ብክነት“ የታለመ የነዳጅ ድጎማን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

በነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ የሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ብቻ  በቀን ውስጥ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ሰባት ሊትር፣ ሚኒባስ 65 ሊትር፣ ሚዲባስ 94 ሊትር፣ ታክሲ 25 ሊትር፣ የከተማ አውቶብሶች 102 ሊትር፣ የመግስት ሰራተኞች ባስ 25 ሊትር አንዲሁም ሀገር አቋራጭ ተሸከርካሪዎች 65 ሊትር ማግኘት ይችላሉ፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.