ዜና፡ መምህር እና ጋዜጠኛ መስከረም አበራ በቁጥጥር ስር ዋለች፤ ባሳለፍነው ሳምንት በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል

በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2/2015 ዓ.ም፡- “ኢትዩ ንቃት” የተሰኘው ዪትዩብ ቻናል መስራች እና ባለቤት፣ የፖለቲካ ተንታኝ መምህር እና ጋዜጠኛና መስከረም አበራ በትላንትናው እለት ወደ 12 ሰዓት አካባቢ በፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ሲቪል በለበሱ በደህንነት አካላት በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ ፍፁም ገብረ ሚካኤል ለአዲስ ስታነዳርድ ገለፁ፡፡

ፍፁም ሁኔታውን ሲያስረዱ “በቁጥር ከአስር በላይ የሚሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች ትላንት ወደ 12 ሰዓት አካባቢ የመኖሪያ ቤታችንን በር አንኳኩ፣ ለብርበራ ነው የመጣነው አሉ፣ የፍርድ ቤት ወረቀት አላቹ ሆይ ብለን ስንጠይቃቸው አልያዝንም እኛ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ነን መታወቂያችንን ማየት ትችላላችሁ አስቸኳይ በሆነ ጊዜ ብርበራ እናደርጋለን፤ ከዚህ በፊት ወረቀት ተሰጥቷችሁ ያውቃል ብለው ጠየቁን  እኛም ተሰጥቶን አይተን ነው ብርበራ የሚደረገው ስንላቸው በቃ ተባበሩን ብለው ጠየቁን ከዛ በርብረው ሶስት ወረቀቶቿን እና የግል ስልክን በኤግዚቢትነት ያዙ፤ ከዛ ወደ 1፡20 ሲሆን አሁን ለጥያቄ ስለምንፈልጋት በቁጥጥር ስር ውላለች ብለው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ይዘዋት ሄዱ” በማለት ተናግረዋል፡፡

መጀመርያ ብርበራ ለማድረግ የመጡ ነበር እንጂ በቁጥጥር ስር የሚያውሏት አልመሰለኝም በነበር የሚሉት ባለቤቷ ከመኖሪያ ቤቷ በተጨማሪ ስቱዲዮ ሄደው ብርበራ ማድረጋቸውን እና ምንም አለማግኘታቸውንም አክለው ገልፀዋል፡፡ ደህና መሆኗን፣ ያደረሱባት ድብደባ እና ጥቃት አለመኖሩን ገልፀውልናል፡፡

የመስከረም አበራ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛሀኝ የፌዴራል ፖሊስ ነው ያለችው ተብለን ወደዛ ስናመራ የፌዴራል እስረኛ ስለሆነች በአደራ ነው የያዝናት ብሎ ማግኘት አልቻልንም ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ በዛሬው እለት ከሰዓት በኋላ ፍርድቤት እንደምትቀርብ ተገልጾልን ብንሄድም ፍርድቤት አላቀረቧትም ሲሉ ጠበቃዋ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

ጋዜጠኛ መስከረም ለእስር ስትዳረግ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም  በቁጥጥር ስር አውሏት ነበር፡፡ ፖሊስ ጋዜጠኛዋ በማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገፅ እና ኢትዮ ንቃት በተሰኘ የራሷ ሚዲያ ህግ መንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ፣ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና በመከላከያ ሰራዊት ላይ እምነት እናዳይኖር ለማድረግ እንዲሁም በአዲስ አበባ የኦሮሚያ መዝሙርና ባንዲራ ጉዳይ ላይ እና በጉራጌ ዞን በተነሳው ግጭት ላይ ቅስቀሳ በማድረግ ወንጀል ጠርጥሯት ክስ ቢመሰረትባትም የ50 ሺህ ብር በዋስትና ከእስር ተፈትታለች።

መስከረም አበራ ግንቦት 12/ 2014 ዓ.ም በፀጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውላ የነበር ሲሆን፣ በወቅቱ ፖሊስ “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እና የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልልን ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት እንደምትሰራ” ጠርጥሬያታለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ በኋላም ፍርድ ቤቱ የቀረበባት ክስ የዋስ መብት የማያስከለክል በመሆኑ በ 30 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንድትፈታ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የየኔታ ትዩብ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ባሳለፍነው ሳምንት ሃሙስ እለት በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ በቁጥጥር ስር ካዋሏት ፀጥታ አካላት ጋር የነበረው ንግግር በስልክ ተቀድቶ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት እየተሰራጨ የሚገኝ ሲሆን ከድምፁ መረዳት እንደሚቻለው በጋዜጠኛዋ ላይ ስድብ እና ድብደባ ተፈጽሞባታል፡፡

በተጨማሪም የአማራ ሚዲያ ማዕከል ዋና አዘጋጅ የሆነው አባይ ዘውዱ በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ መጋቢት 28 2015 ዓ/ም በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ዓቃቢ ህግ “ጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ተልዕኮ ተቀብሎ የመንግስትስ ከፍተኛ አመራሮችን እና ታዋቂ ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሀይል በመናድ ወንጀል ጠርጥሬዋለው ሲል ክስ መስርቶበታል፡፡

ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ በፌደራል የፀጥታ ሃይሎች ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱን ባሳለፍነው ሳምንት የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ በአማራ ሚዲያ ማዓከል(አሚማ) እና በኢትዮ 251 ኦላየን ሚዲያ ላይ ያገለገለ ሲሆን አሁን ላይ  የግሉ ባቋቋመው ሮሓ ኒውስ ሚዲያ ላይ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡

የአማራ ድምፅ ሚዲያ ዋና አርታኢ ጌትነት አሻግሬ በፌደራል ፖሊስ መያዙን አዲስ ስታነዳርድ የስራ ባልደረባውን እና እህቱን በማናገር መዘገቧ ይታወሳል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.