ዜና፡ በጎንደር ከተማ የተደረጉ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ክልከላዎች ተደረጉ፤ በአማራ ክልል በአንዳንድ ከተሞች የከባድ መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ነዋሪዎች ገልጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2 /2015 ዓ.ም፡- ፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በትላንትናው ዕለት ሰልፎች መካሄዳቸውን እና በአንዳንድ ከተሞች በመንግስት የጸጥታ ሀየሎች መካከል ግጭት መፈጠሩን ነዋሪዎች አስታወቁ። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት ከባድ መሳሪያዎች መጠቀሙን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። በቆቦ ከተማ የመድፍ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል። በዛሬው ዕለት በከተማዋ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስተባባሪነት ነገሮች መረጋጋታቸውን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

አብን ትላት ባወጣው መግለጫ በራያ ቆቦ ከተማ ውስጥና በዙሪያው በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ ሲደረግ መዋሉን ገልፆ በከተሞች ውስጥና አቅራቢያ የሚደረግ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።

በትላንትናው ዕለት በተለያዩ በርካታ የክልሉ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄደባቸው ከተሞች አንዱ ጎንደር  ነው፡፡ በጎንደር ከተማ በትላንትናው እለት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የጸጥታ ሀይሎች የተሳተፉበት ተቃውሞ ተስተናግዷል። በባህርዳር ከተማ፣ ደሴ እና ወልድያም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። ከሰልፎች በተጨማሪም የበርካታ ከተሞች መግቢያና መውጫ መንገዶችም በመዝጋት ተቃውሞ መካሄዱን መረጃዎች አመላክተዋል።

በጎንደር ከተማ ሲደረጉ የነበሩ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በዛሬው እለት የከተማው ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የከተማዉን ሰላምና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እንዲቻል  ክልከላዎችን ጥሏል፡፡  

በዚህመ መሰረት በከተማው ያሉ ማንኛውም መጠጥ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች እስከ ምሽቱ 3:00 ሰዓት ዉጭ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተከለከለ ሲሆን በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ 3 እግር ባጃጆች ከንጋቱ 12:00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ዉጭ መንቀሳቀስ ተከልክለዋል።

ከተፈቀደለት የመንግስት የፀጥታ ኃይል ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እና መቶከስ፣ ድምፅ አልባ መሳሪያዎችን ስለታማ የሆኑ እንደ ጩቤ ፣ ገጀራ ፣ አንካሴ ፣ ጦርና ፌሮ ብረት ወዘተ የመሳሰሉትን ይዞ መንቀሳቀስ በክልከላው ተካተዋል፡፡ በህግ የሚፈለጉ ወይም ተጠርጣሪዎችን ሽፋን የሰጠ ፣ የደበቀ ፣ የሀሰተኛ መረጃ ሰጥቶ ያሰመለጠ ፣ የፀጥታ ሀይሎችን የህግ ማስከበር ተልዕኮ ማደናቀፍ ማወክ በህግ ተከልክሏል።

ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን ስብሰባ ማድረግ ፣ ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ተከልክሏል፣ አድማ መቀስቀስ፣ ማድረግና ማስተባበር እንዲሁም መደበኛ ስራን ማስተጓጎል በጥብቅ የተከለከሉ መሆኑን የገለፀው መግለጫው የሠራዊቱን  አልባሳት ከሰራዊቱ አባላት ውጭ መልበስ እንዲሁም   የልዩ ኃይል ፣  የፓሊስ ፣ የፌዴራል ፓሊስ ልብስ መልበስ በጥብቅ ተከልክሏል ብሏል።

የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞጭ ተቃውሞ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በትላንትናው እለት ባስተላለፉት መልዕክት የክልል ልዩ ሀይሎችን እንደገና የማደራጀቱ እንቅስቃሴ ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ የመንግስታቸውን ቁርጠኛ አቋም አስታውቀዋል። ጠ/ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ አካላትን በሁለት ከፍለው ያስቀመጡ ሲሆን በአንድ ጎራ ያስቀመጧቸው አካላት ሳይገባቸው የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ሲለው በመፈረጅ ለማስረዳት እና ለማሳመን ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፤ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡት ደግሞ ሆን ብለው አፍረሽነት ሚና የሚጫወቱ ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን እነዚህንም ተገቢው የሕግ ማስከበር እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በትላንትናው እለት ባስተላለፉት መልዕክት በበኩላቸው የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን በተለየ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እና ለመበተን የተወሰነ ውሳኔ የለም ሲሉ ገልጸዋል።  ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የቴሌቪዢን ጣቢያ ቀርበው ባስተላለፉት መልዕክት ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት እና በክልል መንግሥታት ስምምነት የተወሰነ መሆኑ እና በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀው በአማራ ክልል ውሳኔውን ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን እና ይህንን በተመለከተ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት መካሄዱን አመላክተዋል። አብዛኛው የልዩ ኃይል አባል ውይይቱን አጠናቆ ውሳኔውን  በካምፕ ሆኖ እየተጠባበቀ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ መጋቢት 29 ቀን 2015  በሀገሪቱ ብሔራዊ እና ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠራቸው የቴሌቪዠን ጣቢያዎች ቀርበው በሰጡት ቃለምልልስ የክልል ልዩ ሀይሎችን የመበተኑ ስራ ትጥቅ እንዲፈታም ወይንም እንዲበተን ሳይሆን መልሶ የማደራጀት ስራ ነው፣ ይህም ላለፉት አራት አመታት ስንሰራበት የነበረ የህገመንግስቱ ጉዳይ ነው ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ጀነራሉ በተጨማሪም የክልሎቹ ልዩ ሀይሎች በምርጫቸው መሰረት ወደ መከላከያ ሰራዊት ወይንም ፌደራል ፖሊስ መካተት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

የፌደራል መንግስቱን ውሳኔ እና ተግባራዊነቱን በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በሳለፍነው ሳምንት ውሳኔውን አብን እና ባልደራስ እንደሚቃወሙት በመግለጫዎቻቸው ያሳወቁ ሲሆን ኢዜማ ግን ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው ማለቱ ተዘግቧል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ በፅኑ ተቋውሞታል፡፡ አብን ባወጣው መግለጫ  ከዚህ ቀደም አቋሙን በገለፀበት መግለጫ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ ነው ሲል ስጋቱን መግለፁን አስታውሶ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እና ከአማራ ክልል መንግስት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ እና የክልሉን እና የሃገራችንን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ውሳኔው እንዲከለስ አሳስቧል፡፡

ፓርቲው በትላንትናው መግለጫውም ገዥው ፓርቲ እና የፌዴራሉ መንግስት ስህተቱን ከማረም እና መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ከጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ችግሩን እያወሳሳበ እና ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ እየዳረገው ይገኛል ብሏል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በመግለጫው በመርህ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና ሀገራዊ በሆነ ተክለ ሰውነት በተላበሰ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት እንደሚያምን ጠቅሶ ነገር ግን ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር እና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም ሲል አቋሙን አንፀባርቋል፡፡ ባልደራስ በአቋም መግለጫው የአማራ ክልል መንግሥት ይህን የአማራ ህዝብን ለአደጋ አጋላጭ የሚያደርግ ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ እንዲቃወምና ተግባራዊ እንዳያደረግ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባልደራስ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

የመንግስት ውሳኔ በእርግጥም ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም ሲል ኢዜማ  በውሳኔው መስማማቱን ያመላከተበት መግለጫ አውጥቷ፡፡ ኢዜማ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል ሲል ሃሳቡን አጋርቷል፡፡ ፓርቲው አክሎም የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መግባታቸውን ከልባችን የምንደግፈው ውሳኔ ሆኖ እያለ ፤ አተገባበሩ ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ፣ በተለይም በሀገራችን ሥር ከሰደደው የዘውግ ፖለቲካ ጡዘት አኳያ አፈጻጻሙ በተጠና መልኩ መኾን አለበት ሲል አሳስቧል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.