ዜና፡ ልዩ ሀይል ትጥቅ እንዲፈታም ሆነ እንዲበተን የተላለፈ ውሳኔ የለም፣ መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው፣ ይህም የህገመንግስቱ ጉዳይ ነው – ጀነራል አበባው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ትላንት በሰጡት መግለጫ የክልል ልዩ ሀይሎችን የመበተኑ ስራ ትጥቅ እንዲፈታም ወይንም እንዲበተን ሳይሆን መልሶ የማደራጀት ስራ ነው ይህም ላለፉት አራት አመታት ስንሰራበት የነበረ የህገመንግስቱ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጀነራሉ በሀገሪቱ ብሔራዊ እና ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠራቸው የቴሌቪዠን ጣቢያዎች ቀርበው በሰጡት ቃለምልልስ ፣ የፌደራል መንግስቱን አቋም የሁሉም ክልሎችን ልዩ ሀይልን የማፍረስ ተግባራዊ እንቅስቃሴን በመደገፍ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አክልውም በቃለ ምልልሱ የክልሎቹ ልዩ ሀይሎች በምርጫቸው መሰረት ወደ መከላከያ ሰራዊት ወይንም ፌደራል ፖሊስ መካተት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ይህ የፌደራል መንግስቱ እንቅስቃሴ ከአማራ ክልል ነዋሪዎች ተቃውሞ በማስተናገድ ላይ ይገኛል መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከሆነ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች በርካታ ቁጥር ያለው ነዋሪ ወደ መንገድ በመውጣት ተቃውሞ በማሰማት እና መንገድ በመዝጋት የመከላከያ ሰራዊቱን እንቅስቃሴ ማስተጓጎላቸው ተገልጿል፡፡

አንዳንድ ከአማራ ክልል የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ የተወሰኑ የክልሉ ልዩ ሀይል አባላት የመንግስትን ውሳኔ በመቃወም መኖሪያ ካምፖቻችውን ጥለው መውጣታቸውን አመላክተዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የልዩ ሀይሉ አባላት ወደ መኖሪያ ካምፓቸው ወይንም ወደ ስራ ምድባቸው እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን መልሶ የማደራጀቱን ስራ በትእግስት እንዲጠባበቁም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል በመጀመሪያ ለማን ነው ትጥቅ የሚፈቱት ሁለተኛ ማን ነው ትጥቅ ፍቱ ያለው ከየት ነው ይህ ቃል የመጣው ሲሉ የጠየቁት ጀነራል አበባው እየተከናወነ ያለው እውነታ ልዩ ሀይሉን በህገመንግስቱ መሰረት መልሶ ማደራጀት እና ሌላ መሳሪያ ማስታጠቅ ነው ብለዋል፡፡

እንበትናለን ትጥቅ እናስፈታለን ያለ የለም አላልንም ብለዋል:: እንደገና የማደራጀቱ ስራ በሁሉም ክልሎች እኩል እየተተገበረ መሆኑን ጀነራሉ አስታውቀዋል፡፡አንዱ ክልል በጉልበት የተጠናከረ አንዱን ክልል ደግሞ የተዳከመ ለማድረግ አንሰራም ይህ በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል

የክልል ልዩ ሀይልን አደረጃጀት በብሔር ማንነት መሰረት መሆኑን የተቹት ጀነራሉ ልዩ ሀይሎቹ በጉልበት መከላከያን የሚገዳደሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም አይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏ፡፡
የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት በመኖሪያ ካምፖቻቸው ወይንም በየተመደበበት የሥራ ቦታ ተረጋግቶ በትግስት እንዲጠብቁ ጥሪውን አስተላልፏል።

የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መላው የክልሉን ሕዝብና ልዩ ኃይሉን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም መሆኑንም አስታውቋል፡፡ አክሎም ሁሉም ክልሎች በጋራ የወሰኑት እና ተግባራዊ እያደረጉት እንደሚገኙም ጠቁሟል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.