ዜና፡ ለትግራይ የተላከውን እርዳታ አብዘሃኛውን የዘረፉት የፌደራል መንግስቱ ተጠሪ አካላት እና የኤርትራ መንግስት ሀይሎች ናቸው ሲል አጣሪ ኮሚቴው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2015 ዓ.ም፡- በትግራይ ለተጎጂዎች እንዲዳረስ በሚል የቀረበ እርዳታን መዘረፉን የሚያመላክቱ መረጃዎች ማግኘቱን በግዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት አስታወቀ።

አጣሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ  በትላንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እና በክልሉ መገናኛ ብዙሃን የተላለፈው መልዕክት እንዳመላከተው ለትግራይ ተጎጂዎች የተላከው የምግብ እርዳታ አብዘሃኛው የተመዘበረው በፌደራል መንግስቱ ተጠሪ አካላት እና በኤርትራ መንግስት ሀይሎች ነው ብሏል። ከፌደራል መንግስቱ ተጠሪ አካላት እና ከኤርትራ መንግስት ሀይሎች በተጨማሪ በትግራይ ክልል መንግስት አካላትም በዘረፋው መሳተፋቸውን መግለጫው አካቷል።  በትግራይ ለተጎጂዎች ተብሎ የቀረበውን እርዳታን ላልታለመለት አላማ በማዋሉ ሂደት 186 ተጠርጣሪዎች መሳተፋቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ ሲል የገለጸው አጣሪው ኮሚቴ ከነዚህ ውስጥ ሰባት ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አስታውቋል።

ህብረተሰቡ በቀሪ ስራዎች ላይ እንደተለመደው ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪ ያቀረቡት የአጣሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር እና የግዜያዊ አስተዳደሩ የጸጥታ እና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በህግ ስራ ለማዋል እና ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አጣሪ ኮሚቴው እስካሁን ባደረገው ክትትል በኤርትራ ሰራዊት 28ሺ 880 ኩንታል ስንዴ፣ 43ሺ 200 ሌትር ዘይት እና አንድ ሺ 440 ኩንታል አተር መዘረፉን አስታውቋል። በፌደራል መንግስት አካላት ደግሞ 43ሺ 196 ኩንታል ስንዴ፣ 129ሺ 585 ሊትር ዘይት እና 4ሺ 187 ኩንታል አተር መሀረፉን አመላክቷል። በትግራይ ክልል መንግስት አካላት የተዘረፈው ደግሞ 14ሺ 317 ኩንታል ስንዴ፣ 42ሺ 759 ሊትር ዘይት እና አንድ ሺ 424 ኩንታል አተር መሆኑን አካቷል።

በእርዳታ እህል ዘረፋው ላይ የተፈናቃይ ካምፕ አስተባባሪዎች እና የእርዳታ ሰራተኞችም ተሳታፊ መሆናቸውን የአጣሪ ኮሚቴው አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና ህወሓት በትላንትናው ዕለት ለአራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ባጠናቀቀበት ወቅት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ሲካሄድ የነበረው የእርዳታ አቅርቦት መቋረጡን ተቃውሟል። የእርዳታ እህል የማቋረጡ ውሳኔ በረሃብ የሚሰቃየውን የትግራይ ህዝብ በሞት ለመቅጣት የተወሰነ ውሳኔ እንጂ ጥፋተኞችን ለመቅጣት አይደለም ሲል ተችቷል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር በመምከር እርዳታውን ለማስጀመር በሚያደርገው ጥረት እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በጀመረው ስራ ፓርቲው ትብብሩን እንደሚያጠናክርም አስታውቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.