ዜና፡ ህገ-ወጥ ግንባታን የማፍረስ ተግባር በመስጂድና ሸገር ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ አለመሆኑን እና ከ600 በላይ ከተማዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23/ 2015 ዓ.ም፡- እየተከናወነ ያለው ህገ-ወጥ ግንባታን ማፍረስ ተግባር በመስጂድና ሸገር ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ አለመሆኑንና በህገ-መንግስቱ እና በህግ አግባብ መሰረት በክልሉ ከ600 በላይ ከተማዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሃይሉ አዱኛ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ህገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ ተግባሩ በጥንቃቄ የሚታይና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል መክሮበት ቀን ገደብ ተሰጥቶት በእራሱ እንዲያፈርስ የሚደረግና ግልፅነት ባለውና ህግን በተከተለ መልኩ የሚከናወን ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሃላፊው በአፈፃፀሙ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ካሉም በውይይት ለመፍታትና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር መግባባት ለመፍጠር መንግስት በሩ ክፍት ነው ብለዋል።

በማከልም የክልሉ መንግስት በሀገሪቱና በክልሉ ፀጥታና መረጋጋትን ለማስፈን ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ መንግስት በመስጂዶች ላይ ብቻ እንዳነጣጠረ አድርገው ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ፅንፈኞችን  እንዲቃሙ አሳስበዋል። በተጨማሪም መንግስት ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ጠቁመው የሀይማኖት ተቋማትም  የሃይማኖት ሽፋን  በማድረግ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲቃወሙም ጥሪ አቅርበዋል።

ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ/ም ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ በተካሄደ የተቃውሞ ሰለፍ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይታወቃል፡፡

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ግቦት 14 ባወጣው መግለጫ “መንግስት የመስጂድ ፈረሳ ተግባር በአስቸኳይ አቁሞ ያለውን ችግር በመክክር እንዲፈታና የፈረሱ መስጅዶች በአስቸኳይ እንዲተካ” መቀየቁ ይታወሳል፡፡

ከኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በተጨማሪም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ግንቦት 10 2015 ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ ህገ-ወጥ በሚል መስጂዶች እየፈረሱ መሆናቸውን በመግለፅ መፍትሄ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጅ ኢብሪሒም በደብዳቤያቸው የመስጂድ ፈረሳ ጉዳይ በከተማ አስተዳደሩ «ሕገ ወጥ» ስለተባለ ብቻ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን የሕዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖቱ ዋንኛ ሕልዉናዉ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጻፍነው ደብዳቤም እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልፀዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.