ዜና፡ የመስጊድ ፈረሳና በዕምነቱ ተከታዮች ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23/2015 ዓ.ም፡- መንግስት በኦሮምያ እና አዲስ አበባ በእስልምና ዕምነት ተቋማት ላይ እየፈጸመ ያለው የመስጊድ ፈረሳና በዕምነቱ ተከታዮች ላይ እየፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ጠየቀ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ። በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የቤት ፈረሳ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሱት ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር  እየተከናወነ ያለው የቤት ፈረሳ እንቅስቃሴ የሃይማኖት ተቋማትንም የጨመረ መሆኑን የጠቆመው ኢሰመጉ ከኦሮሚያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባገኘው የቃል መረጃ መሰረት በእዚህ ፈረሳ እንቅስቃሴ ምክንያት ከ19 በላይ መሰጊዶች መፍረሳቸውን ለመረዳት ችሏል ብሏል፡፡ ይህ የቤትና የዕምነት ተቋማት የፈረሳ እንቅስቃሴ ህዝቡን በማወያየትና ተተኪ ቦታ በመስጠት መከናወን የሚገባው ድርጊት ሆኖ ሳለ የአፈጻጸም ክፍተት ባለበት ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ሲል ኮንኗል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የመሲጊዶችን የማፍረስ እንቅስቃሴውን ተከትሎ በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ በ18/09/2015 ዓ.ም ከጁምአ ሶላት በኋላ ድርጊቱን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የመንግስት የጸጥታ አካላት በወሰዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ንብረት መውደሙንና በእምነቱ ተከታዮች ላይ እስራት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉት አስታውቋል።

የሰብአዊ መብት ጉባኤው በመግለጫው ባቀረበው ባቀረበው ጥሪ መስጊዶችን የማፍረስ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት ከእምነቱ ተከታዮችና መሪዎች ጋር ተገቢው ውይይትና መግባባት ላይ እንዲደረስ ጠይቋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ በ18/09/2015 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ባደረገ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የፈጸሙ የመንግስት የጸጥታ አካላትን መንግስት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ እየተፈጸሙ ስላሉ የቤት ፈረሳና የግዳጅ ማፈናቀል እንቅስቃሴዎች ዝርዝር ዘገባን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግና በእዚህ ዘገባ ላይ የመስጊዶች ፈረሳውንም ተጨማሪ መረጃዎችን በማሰባሰብ የሚያቀርብ በመግለጫው አመላክቷል።

በተያያዘ ዜና በኦሮምያ ክልል እየተከናወነ ያለው ህገ-ወጥ ግንባታን ማፍረስ ተግባር በመስጂድና ሸገር ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ አለመሆኑንና በህገ-መንግስቱ እና በህግ አግባብ መሰረት በክልሉ ከ600 በላይ ከተማዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሃይሉ አዱኛ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።  ህገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ ተግባሩ በጥንቃቄ የሚታይና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል መክሮበት ቀን ገደብ ተሰጥቶት በእራሱ እንዲያፈርስ የሚደረግና ግልፅነት ባለውና ህግን በተከተለ መልኩ የሚከናወን ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.