አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8 2015 ዓ.ም፡- የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በኢንቨስትመንት እና በአብረን እንስራ ስም ተጨባጭና የተሟላ መረጃ ሳይሰጡ ከፍተኛ ገንዘብ ከህብረተሰቡ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ገልፆ ከመሰል የማጭበርበር ድርጊት ራሱን እንዲጠብቅ አስቀነቀቀ፡፡
አገልግሎቱ ሰኔ 6 ቀን ባወጣው አጭር መግለጫ በስም ያልጠቀሳቸው አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ገንዘብ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብም እጅግ አትራፊ የሆነ የግብርና እና የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራታቸውን በመግለፅ ቅንጡ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት እንዲሁም አክሲዮን በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚችሉ በተለያዩ መንገዶች እያስተዋወቁና ገንዘብ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተገንብያለሁ ብሏል፡፡
አገልግሎቱ ይህን ያለው ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ከህብረተሰቡ ገንዘብ እየሰበሰቡ ባሉ ድርጅቶች ላይ ቅሬታዎች በመራከታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ይህንን ተከትሎ ዘፀአት ሪል አስቴት ትላንት ሰኔ 7 ባወጣው መግለጫ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ ማህበሩን የማይወክል መሆኑን ገልፆ የማህበሩ ኮሚቴ የተደረሰበትን የስራ ሂደቱን በቅርብ ያስታውቃል ብሏል፡፡ አባላቱም ከሀሰተኛ መረጃ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትም በበኩሉ በኢንቨስትመንት ስም የሚፈፀሙና ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችንም መከላከል እንደሚገባ ጠቅሶ ህብረተሰቡ ከመሰል ድርጊቶች ጋር ተያይዞ ሊፈፀም ከሚችል መጭበርበር ራሱን እንዲጠብቅ፣ የጥንቃቄ እርምጃም እንዲወስድ አሳስቧል።
በተጨማሪም አገልግሎቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ከተለያዩ አካላት የፋይናንስ ወንጀል ነክ መረጃዎች በመቀበል፣ በመሰብሰብና በመተንተን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት በማሰራጨት እንዲሁም በመሰል ጉዳዮች ላይ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታወውቋል።አስ