አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 18/2014 – ከ300,000 በላይ ተፈናቃዩች በአፋር ክልል በ14 መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ቢገኙም ከፌደራል መንግስት የሚደረገው ድጋፍ አጥጋቢ አለመሆኑን የአፋር ክልል የአደጋ እና ስጋት ቁጥጥር ሀላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።
በቀን ከ200 -300 ተፈናቃዩች ወደ ተፈናቃይ መጠለያ እንደሚገቡ የተናገሩት አቶ መሀመድ ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት የተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መቷል ብለዋል። “በአሁኑ ሰአት በርካታ ህፃናትና ሴቶች በመጠለያ ውስጥ አሉ። የክልሉ መንግስት ባለው አቅም እርዳታ እያደረገ ቢሆንም በፌደራል መንግስት የሚደረገው ድጋፍ አጥጋቢ አይደለም። የ5 ወረዳ ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ተፈናቅለው ይገኛሉ። 300,000 ያልነው በእኛ ስር ተመዝግበው የሚገኙትን ብቻ ነው” ይላሉ።
ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ተፈናቃዩችን ወደ ነበሩበት መኖሪያ መመለስ እንደማይቻል የተናገሩት አቶ መሀመድ የተባበሩት መንግስታት ሆነ ሰብአዊ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች የሚለግሱት እርዳታ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሱልጣን ያሲን በአፈር ክልል በበራህሌ ወረዳ ነዋሪ የነበረ ሲሆን ከ10 የቤተሰቡንየ አባላት ጋር 100 ኪሎ ሜትር በእግራቸው ተጉዞ አሁን በመጠለያ ይገኛል። ” በጣም ነው የሚያሳዝነው። እኛ ጦርነት ውስጥ የገባነው ተገደን ነው። ማንም ፈልጎ አይገባም ግን የአፋር ህዝብ ይለያል። መንግስት ምግብም ሆነ የቁሳቁስ እርዳታ እያደረገልን እይደለም ማለት ይቻላል። መጀመሪያ አብረናችሁ ነን ሲሉ የነበሩ ሁላ አሁን ከእኛ ጋር የሉም። እኛ ኢትዩጵያዊ ነን፣ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀምብን የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ ሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ጠፉ” ብለዋል። የአፋር ንፁሀን ሰዎች ሲገደሉ ዝም መባሉም እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
ሌላዋ ከመኖሪያዋ ተፈናቅላ በቡቲ ወረዳ የምትገኘው ወ/ሮ ፋጡማ ንግግሯን የጀመረችው ‘አላህ ፍርድ ይሰጠናል’ ስትል ነው። “መንግስት ባለበት አገር ከቤታችን ተባረን በየመጠለያው ነው ያለነው። ህፃናት ይዘን ህክምና ከፍለን ነው ምንታከመው። የሚሰጠን እርዳታ እራሱ በጣም ትንሽ ነው። ልጆቼ በየግዜው ነው የሚታመሙት :: ወደ ቤቴ ተመልሼ ኑሮዬን እንደገና መጀመር እፈልጋለው። እኔ ሴት ነኝ በዛ ላይ እናት ልጆቼን ይዤ በሰላም መኖር ነው የምፈልገው:: በስልጣን ላይ የተቀመጡት ልጆታቸው እየበሉ የእኔ ልጆች እየተራቡ ሳይ ለአላህ እያለቀስኩ እነግረዋለው” ብላለች። ምን ያህል ተፈናቃዩች እንዳሉ የተጠየቀችው ፋጡማ መንግስት የሚያውቀው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እርሷን ጨምሮ ተመዝግበው ያሉትን በቻ መሆኑን ጠቅሳ በርካታቶች ደግሞ በየበርሀው ተበታትነው እንደሚገኙ አስረድታለች። “የእኔ ጎረቤቶች አሁን አልመጡም። ግመሎቼን እና ፍየሎቼን ጥዬ አልሄድም ብለው እዚያው ናቸው። ምን እንደሆኑ እንኩዋን መረጃ የለኝም” ብላለች::
በተቃራኒው በአፋር ክልል 1.3 ሚሊየን ህዝብ ድጋፍ እንደሚፈልግ የገለፁት የብሄራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ “በአፋር ክልል የአለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ እያደረገ ሲሆን ከዚያ በተጨማሪ የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ መንግስት እንዲሁም ግለሰቦች እርዳታ እያደረጉ ነው” ብለዋል። በአሁኑ ሰአት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት መልካም መሆኑን እና ክልሎች የተሰጣቸውን እርዳት አብቃቅቶ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል ::
የአፋር ክልል አደጋና ስጋት ቁጥጥር ሃላፊ አቶ መሀመድ “ከአስር ቢሊየን ብር በላይ መሰረተ ልማቶች እንደወደሙ ገልፀው የአለም አቀፍ ድርጅቶች የህውሀት ጦር ከያዘው ከአፋር ክልል ለቆ እንዲወጣ እና ጦርነቱን እንዲያስቆም ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በአፋር ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፉ በቂ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። የአፋር ህዝብ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዳስታወቀው ዕርዳታ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እየደረሰ እንዳልሆነ እና የምግብ እቃዎች በመጋዘን ውስጥ ተከማችተዋል።
ፓርቲው የእርዳታ አቅርቦቱን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል በብቸኝነት ይዞታል ሲል መንግስትን ወቅሷል። “የሚደረጉት ድጋፎች ከፖለቲካዊ ገጽታ ግንባታ ባለፈ ለእውነተኛ ተጎጂዎች እየደረሱ አይደለም የሚል ቅሬታ እየቀረበብን ነው” ሲልም ፓርቲው ገልጿል።አስ