ትንታኔ፡- ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ይገቡ በነበሩ 38 ምርቶች የተጣለው የውጭ ምንዛሪ እገዳ ጫና እያሳደረብን ነው – ነጋዴዎች

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

ዲስ አበባ፣ ጥቅምት15/ 2015 ዓ.ም ፡- መንስግስት ከውጭ ይገቡ ለነበሩ 38 ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ ላልተወሰነ ግዜ የጣለውን እገዳ ተከትሎ የዕለት ተለት ኑሯቸው ከምርቶቹ ጋር ተያያዠነት የነበራቸው ነጋዴዎች ላይ ጫና እያሳደረባቸው መምጣቱን በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች አስታወቁ፡፡

መንግስት 38 ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች እና ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ያደረገው ክልከላ ከጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡

ምርቶቹ የብሄራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጥናት የተለዩና ለህዝብ ይፋ የተደረጉ ሲሆን መንግስት እገዳ ማድረግ ያስገደደው የውጭ ምንዛከሚፈቀድላቸው ምርቶቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሆነው ባለመገኘታአውና የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የውጭ ምርቶች በቂ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነው ተብሏል።

ከዚህም በላይ ምርቶቹ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት እንደሆኑ በመገንዘብ መንግስት እገዳው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ መወሰኑን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢና ዋና ኢኮኖሚስት ፈቃዱ ድጋፌ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

እገዳ የተጣለባቸው መጠጦች (ውስኪ፣ ቢራ እና ሌሎች አልኮል መጠጦች)፣ የፍራፍሬ ጭማቂ እና የታሸጉ ፍራፍሬዎች አንዲሁም ከፍራፍሬ የተዘጋጁ ጃሞች እና የድንች ጥብሶች፣ ማስቲካ፣ ቸኮሌት፣ ውሃ፣ ሲጋራ፣ የገበታ ጨው፣ የዶሮ ስጋ፣ የአሳማ ስጋ፣ ቱናዎች፣ ሰርዲኖች እና ሌሎች የአሳ ምርቶች፣ ሰው ሰራሽ ማጌጫዎች፣ የእጅ፣ የግድግዳ እና የጠረጴዛ ሰዓቶች፣ ዣንጥላዎች፣ምንጣፎችና መሰል ቁሳቁስ እንደተካተቱ ተገልጧል፡፡

በግለሰቦች ኤል ሲ ተከፍቶባቸው የሚገቡ መኪናዎች እና ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች እገዳው የሚመለከታቸው ሲሆን በኤሌክትሪክ የሚሰሩትን ተመሳሳይ ምርቶች አያካትትም፡፡ ለባንኮች አዲስ ኤል ሲ እንዳይከፍቱ ደብዳቤ መሰራጨቱንም ምክትል ዋና ገዢው ገልጸዋል፡፡

“በምናስገባቸው የመዋቢያ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ስለተደረገብን እኛም ጭማሪ አድርገናል”

አዲስ (ስሟ የተቀየረ)

ውሳኔውን ተከትሎ መንግስት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ያደረገባቸው ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ተስተውሏል፡፡ ለአብነት ያክልም በመጠጦች ዋጋ ላይ ከ 1500 እስከ 2500 ብር የጭማሪ ልዩነት ታይቷል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ በጉርድ ሾላ አካባቢ ወደ ሚገኙ የመዋቢያ ቁሳቁሶች መሸጫ ሱቆች በመሄድ ከሻጮች እና ሸማቾች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ አዲስ (ስሟ የተቀየረ) በጉርድ ሾላ አካባቢ የመዋቢያ ሱቅ ባለቤት ስትሆን በዘርፉ ላይ ስላለው የዋጋ ግሸበት ስታስረዳ “በምናስገባቸው የመዋቢያ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ስለተደረገብን እኛም ጭማሪ አድርገናል” ብላለች፡፡

አዲስ አያይዛም አሁን ያለው ሁኔታ የዋጋ ማናር ብቻ ሳይሆን የሚንፈልገውን እቃ አለማግኘትም ነው፡፡ ቀደም ሲል ዋጋ ቢወደድም የፈለግነውን ዓይነት እቃ መርጠን የመግዛት እድሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ማማረጥ ቀርቶ የሚንፈልጋቸው እቃዎች ገበያ ላይ የሌሉ በመሆኑ ስራችን ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ትናገራለች፡፡

ማክዳ ገብረመድህን ራሷንና ቤተሰቦቿን የምታስተዳድረው በውበት ሳሎን ስራ ሲሆን መንግስት ያስተላለፈው ውሳኔ በዚህ የስራ ዘርፍ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅእኖ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ትላለች፡፡

ስራውን የሚናከናውነው ከውጭ በሚገቡ ቁሳቁሶች በመሆኑ አሁን የተደረገውን እገዳ ተከትሎ እጥረት በማጋጠሙ በተወሰነ መጠን ገበያ ላይ ያሉት ላይም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ ስራውን ማስቀጠል አልቻልንም ያለችው ማክዳ እገዳው ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረባቸው ትናገራለች፡፡

“ይህን የመዋቢያ ቤት የከፈትኩት በቅርብ ግዜ ነው፡፡ አሁን ላይ እያጋጠመ ያለው እጥረት በዚህ ከቀጠለ ለቤት ኪራይ እና ለሰራተኞች የምከፍለው ክፍያን ማግኘት ስለማንችል ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃችን አይቀርም” ያለችው ማክዳ መንግስት መፍትሄ ሊፈልግልን ይገባል ትላለች፡፡

“የተከለከለ ምርት ከየት አመጣችሁ በሚል ሰበብ አላስፈላጊ ክፍያ ሊጠይቁ ስለሚችሉ ነጋዴውም የከፈለውን ለማካካስ በናረ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዳል፡”

የምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው አለሙ

ሄለንም በአካባቢው በተመሳሳይ ስራ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሌሎች ምርቶች በተለየ መልኩ በውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶች ላይ ጭማሪ መደረጉን ጠቅሳ በተለይ ደግሞ በዲዮዶራንት፣ ሽቶና ሊፒስቲክ ላይ ከ250 ብር በላይ ጭማሪ መደረጉን አስረድታለች፡፡

አንድ ሳሙና ከ100 ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ያስገነዘበቸው ሄለን ነጋዴዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ያለ አግባብ ዋጋ እየጨመሩ በመሆኑ መንግስት ከትትል ማድረግ ይኖርበታል ብላለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው አለሙ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት የወሰነው ውሳኔን ተከትሎ የዋጋ ንረት እና የምርቶች እጥረት እንደሚከሰት ጠቁመው ምርቱ በገበያ ውስጥ ቢኖርም ከውጪ እንዳይገባ በመከልከሉ ሻጮች ዋጋውን ስለሚያኑሩት ችግር መፈጠሩ አይቀርም ያሉት ኢኮኖሚስቱ የውሳኔው ተፈፃሚነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

አቶ አጥላው አያይዘውም “የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት መንግስት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ያደረገባቸው ሸቀጦች እና ምርቶች ለህግ አስፈፃሚዎች ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራሉ የተከለከለ ምርት ከየት አመጣችሁ በሚል ሰበብ አላስፈላጊ ክፍያ ሊጠይቁ ስለሚችሉ ነጋዴውም የከፈለውን ለማካካስ በናረ ዋጋ ለመሸጥ ይገደዳል፡፡” ብለዋል፡፡

አንዳንድ ለህግ ታማኝ ያልሆኑ ባለስላጣናት ባሉበት አገር ውስጥ የሚወ ህግ ለተወሰነው አካል የሚሰራ ለሌላው ወገን ደግሞ የማይሰራ ሊሆን ይችላል ያሉት ሙሁሩ በዚህ ሁኔታ ዋጋ ይወደዳል እንጂ እቃዎቹ መምጣታቸው አይቀርም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢኮኖሚስቱ አያይዘውም ለዚህ ዋነኛው መፍትሄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ወስት ምርቶች ለመተካት ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ምሁራን የገንዘብ ግሽበትን እና የጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር የተዘረጉ አዳዲስ አሰራሮች እና የቁጥጥር መንገዶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ሆኖም የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ተጨማሪ ስራዎች መከናወን እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስትንግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ዶክተር መኮንን ካሳሁን እንዳሉት የተዘረጉት አዳዲስ አሰራሮች በተለይ በባንኮች እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሬ ልዩነት ማጥበብ የሚችሉ እና የውጭ ምንዛሬ ክምችትንም የሚያሻሽሉ ናቸው።

የኢኮኖሚክስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ጥምቀቴ አለሜ በበኩላቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከተከለከሉት የእቃ አይነቶች የሚገኘው ውጤት እንደ ሀገር ከሚፈለገው ውጤት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ ተጨማሪ የቅንጦት ምርቶች ላይ እገዳው መቀጠል አለበት።

የቁጥጥር ስራው መጠንከር በራሱ አዳዲስ የህገወጥ መንገዶች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ስለሚችል አስቀድሞ መፍትሄዎችን ማበጀት እና የሀገር ውስጥ ምርት ማሳደግ ይገባልም ብለዋል ምሁራኑ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.