እዲስ አበባ፣ ጥር 9/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከግዜ ወደ ግዜ እየባሰበት መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በተለይ ሰዎች በጅምላ የሚገደሉበት በቁማቸው በእሳት የሚለበለቡበት በስቅላትና በድንጋይ ተወግረው የሚገደሉበት ሁኔታ መከሰቱ እንደ ኢትዮጵያ ላለች በመቻቻልና በአብሮኖት ተጠቃሽ የነበረች አገር እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደ ህዝብና እንደ አገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡ የአዲስ ስታንዳርዱ ሞላ ምትኩ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ም/ ዋና ኮሚሽነሯ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪ በሰብአው መብት አያያዝ ትምህርት ደግሞ ሁለተኛ ድግሪ ያገኙ ሲሆን ወደዚህ ሃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት የሴቶችን እና የህፃናትን መብቶች እነደዚሁም በዲሞክራሲ ዙሪያ በሚሰሩ የተለያዩ ድርጅቶች ለ25 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከኮሚሽኑ ገለልተኛነት እና ከተለያዩ ወገኖች በሚነሱበት ቅሬታዎች ዙሪያ ያደረጉት ሙሉ ቃለምልልስ እንደሚከተለው ቀርበቋል፡፡
ስታንዳርድ ፡ – በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ባጭሩ ቢያብራሩልን?
ራኬብ፡ – የሰብአዊ መብት ኮሚሽንሪፎርም እንዲደረጉ ከተያዙ ተቋማጥ አንዱ ነው፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ተቋሙን የሚመሩ ኮሚሽነሮች ከማንኛውም የፖለቲካ አባልነት ነፃ የሆኑና ለማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውግንና የሌላቸው በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዘርፉ ትምህርትና ልምድ ያላቸው ሆነው አመራረጣቸውም ነፃ ሆኖ እንዲከወን የተደረገበት ሁኔታ ነው፡፡ ከዚያም ቀደም ሲል የነበሩ ጠንካራ ስራዎችን ለማስቀጠልና መስተካከል የሚገባቸውን በመለየት ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት ተቋሙን የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡የሴቶች የህፃናት የአረጋዊያን እና የአካል ጉዳቶኞችን ሰብአዊ መብት የሚከታተሉ ራሳቸውን የቻሉ ዘርፎች በማደራጀት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ስለሚፈፀሙ እነዚህ ላይ ምርመራ በማድረግ ተጎጂዎች መፍትሄ እንዲሰጣቸው እና ክስተቶቹ ዳግም እንዳይፈፀሙ ለማድረግ አስፈላጊውን ምክረ ሃሳብ የመስጠት ስራም እያከናወነ ይገኛል፡፡ ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት ከሰብአዊ መብት መከበር ጋር ተያይዞ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ሆኖም ግን ገና በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርብናል፡፡ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጋር የጣምራ ምርመራ ተደርጎ ምክረ ሃሳቦች ተሰጥተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ስምምነቱ ተፈፅሞ በምክረ ሃሳቡ መሰረት በርካታ ክትትልና የአቅም ግንባታ እየተተገበሩ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ምክረ ሃሳቦች ደግሞ እየተከታተልን እንዲፈፀሙ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – ይህ አሁን ያነሱት ከተባበሩት መንግስታት ቢድን ጋር አደረግነው ያሉት ምርመራ እና ሪፖርተ በሁለቱ ወገኖች ተቀባይነት አግኝቷል እንዴ?
….. ነገር ግን በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የትግራይ ህወሓት እና የኤርትራ መንግስት ምክረ ሃሰቡን አልተቀበሉም፡፡ ምክረሃሳቡን በሚቀበልበት ደረጃ ግፊት እያደረግን ነው፡፡
ራኬብ
ራኬብ፡ – በሁለቱ ወገኖች አይደለም፡፡ ምክረ ሃሳቦቹ በአብዛኛው መፈፀም ያለባቸው በገዢው መንግስት በኩል ነው፡፡በርካታ ስራዎች መሰራት ያለባቸው በአቃቢ ህግ መደረግ ያለበት የወንጀል ምርመራዎች እና ክስ የማቅረብ በርካታው አፈፃፀም የሚከናወነው በመንግስት በኩል ነው፡፡እኛ መንግስት ያንን ተቀብሎ እያደረገው ያለውን አፈፃፀም እየተከታተልን ነው፡፡ ነገር ግን በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የትግራይ ህወሓት እና የኤርትራ መንግስት ምክረ ሃሰቡን አልተቀበሉም፡፡ ምክረሃሳቡን በሚቀበልበት ደረጃ ግፊት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ደግሞ ስምምነቱም ስለተፈፀመ ፍትሃዊ ሽግግር በስምምነቱ ስለተካተተ እነሱም ምክረሃሳቡን የሚቀበሉበት ሁኔታ እየተከታተልን እንገኛለን፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – የጎደለውን ለማወቅም ሆነ ለምን በሁሉም ወገን ተቀባይነት እንዳላገኘ ለማወቅ ምን አድርጋችህዋል?
ራኬብ፡ – እሱን እነሱን መጠየቅ ነው የሚሻለው፡፡ ነገር ግን እንዳልኩት በዋናነት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ያንን መቀበሉን እንደ ትልቅ አወንታዊ ሂደት ነው የሚንወስደ ምክንያቱም በባለቤትነት አብዛኛውን ምክረሃሳቦች ማስፈፀም ያለበት ወገን እሱ ስለሆነ፡፡ ላለመቀበል ምክንያታቸው እንግዲህ ከሚሽኑ ገለልተኛ አይደለም በሌላ ወገን መታየት አለበት የሚለው እንዳለ ሆኖ አሁን ግን የስምምነቱ መፈፀም በሰነዱ አንዱ ምክረሃሳብ ነበር፡፡ከዚህ አኳያ ምክረ ሃሳቡ እየተፈፀመ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፍትሃዊ ሽግግር በስምምነቱ የተካተተ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ እየፈፀሙ አይደለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – እስካሁን በተደረጉ ምርመራዎች መሰረት በአገሪቱ የተፈፀሙ ዓበይት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምን ምን ናቸው?
ራኬብ፡ – በአገሪቱ እየተፈፀሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ፣ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡አንዱ ከአንዱ ለመለየት ወይም ይሄ ከሌላው ግዙፍ ነው ለማለት ሳይሆን በዋናነት ከግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ናቸው፡፡ የርካታ ሰዎች መሞት፣ ለአካል ጉዳተኞች መዳረግ፣ የንብረት መጥፋት፣ የመሰረተ ልማት መውደም፣ የትምህርት እና የጤና መብት መስተጓጎል፣ የአገልግሎት መቋረጥ፣ የመንቀሳቀስ እገዳዎች፣ የመገናኛ መሰረተ ልማቶች መውደም እና ሌሎች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡
….. በሴቶችና በህፃንት ላይ የሚደርሱ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በስፋት ሲነገር የነበረው የወሲብ ጥቃት በስፋት ተፈፅሟል፡፡ ተጠቂዎች የሚያስፈልጋቸው አግልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡
ራኬብ
በተለይ ደግሞ በዓለም ደረጃ አንደኛ ያደረገን የመፈናቀል ሁኔታ አለ፡፡ በርካታ ሰዎች በስፋት ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ከመፈናላቸው ጋር ተያይዞ ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘታቸው ለተራዘመ ችግር የታደረጉም አሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በሴቶችና በህፃንት ላይ የሚደርሱ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ፡፡ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በስፋት ሲነገር የነበረው የወሲብ ጥቃት በስፋት ተፈፅሟል፡፡ ተጠቂዎች የሚያስፈልጋቸው አግልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ እንዳልኩህ የአካል ጉዳተኞች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ በአገሪቱ የነበረው የአካል ጉዳተኛ ቁጥር በውል አናውቀውም አሁን ደግሞ ተጨማሪ ተፈጥረው ከደረሰባቸው ጉዳቶች የሚያገግሙበት አግልግሎት አያገኙም፡፡ በአገራችን አካታች የሆነ ስርዓት ባለመኖሩ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ ነው፡፡ እንደዚሁም አረጋዊያን ለበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይዳረጋሉ፡፡ ተደራሽነት ባለመኖሩ አገልግሎት የማያገኙበት ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ ከግጭት ጋር በተያያዘ የትምህርት እን የጤና መብት ጥሰቶች ተከስተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – ኮሚሽኑ ከመንግስትና ከፖለቲካ ተፅእኖ አልተላቀቀም፡፡ ራሱን ችሎ በሃላፊነት የሚሰራ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ኢሰመኮ ምን ያህል ገለልተኛ ነው ብለው ያምናሉ?
ራኬብ፦ ለገለልተንነት አንዱ ተቋሙን አመራሮች ማለትም ኮሚሽነሮች ከፖለቲካ አባልነትና ውግንና ነፃ መሆናቸው በመሆኑ ይህ ተደርጓል፡፡ በምርጫ ወቅትም አንዱ መስፈርት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ትምህርትና ልምድ ያላቸው በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን በአመራርነት ማምጣት ስለነበር እሱ ተደርጓል፡፡ ሁላችንም በአመራር ደረጃ በተቋሙ ያለን አመራሮች በዚያ መልክ የመጣን በመሆኑ መነሻችንም መድረሻችንም የሰብአዊ መብት ማስከበር ማስጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ነገር አንደኛው ወገን ተደሳች ሊሆን ይችላል በሌላው ደግሞ ልላው ደስተኛ እየሆነ ካልሆነ በስተቀር ወገንተኛ ሆነን አይደለም፡፡ ወገንተኛም ከሆንን የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ተጎጂዎችን ድምፅ ይዘን ወገንተኛ ሆነን የእነሱን ድምፅ ለማሰማት የእነሱን ብሶት ለማሰማትና የደረሰባቸውን ጉዳት ለማሰየትና ለመሰነድ ይሆናል እንጂ ለማንም ወገንተኛ ሆነን አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ስራችን መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው፡፡ መሬት ላይ ባለው መረጃ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምዘና መሰረት ነው ስራችንን እየሰራን ያለነው፡፡ ለዚህ ነው ሪፖርት ስናወጣ ግዜ የሚወስድብን ወዲያው እንደተሰማ ሳይሆን ሪፖርት የሚናደርገው ቦታው ላይ ደርሰን፣ ከተለያዩ ወገኖች ያለውን መረጃና ሰብስበን፣ አመሳክረን፣ አረጋግጠን ነው ሪፖርት የሚናደርገው፡፡ ነገር ግን ለማንኛውም ወገን አድልተን አይደለም ስራችን የሚወስነው መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – ቅሬታዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ችግሮች ላይ በፍጥነት ሪፖርት ስታደርጉ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ የመዘግየትና የመታሸት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ራኬብ፦ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ነው ሪፖርትን በፍጥነት ለማውጣና ለማዘግየት ምክንያት የሚሆነን፡፡ አብዛዛኛውን ግዜ በግጭት ላይ ያለ አካባቢ ከሆነ ቦታው ላይ ደርሰን ምርመራ አድርገን ሁኔታዎችን ባግባቡ አጣርተን ሪፖርት ለማውጣት የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙ የመዘግየት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ በቦታው ያለውን ሁኔታ በትክክል ሳንመረምር በማህበራዊ ሚዲያ ስለተለቀቀ ብቻ ብለን ሪፖርት አናወጣም፡፡ ትልቁ የመዘግየት ምክንያት ቦታው ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡ ሌላው የተቋማችን አቅም ይወስነዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ጨምሮ ያለን አጠቃላይ ስታፍ 360 አካባቢ ነው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጥልቀትና በስፋት መርምሮ አረጋግጦ ሪፖርት ለማውጣት እንቸገራለን፡፡ ስለዚህ ሪፖርቱ ሊዘገይ ይችላል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አሁን ከሰላም ስምምነቱ በህዋላም ሳይቀር የኤርትራ ወታደሮች በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ እንደሆነ የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ኢሰመኮ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን የሰራው ነገር አለ?
ራኬብ፡- በቦታ መገኘት ስላልቻልን ያንን ማጣራት አልቻልንም ስለዚህ ለግዜው ማለት የምችለው ነገር የለም፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – በትግራይና በፌዴራል መንግስት በተደረገው የሰላም ስምምነት ሂደት ፍትሃዊ ሽግግርን እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል? በዚህ ረገድስ ምን እየተደረገ ነው?
ራኬብ፡- ፍትሃዊ ሽግግር የሚባለው በጣምራ ምርመራችን ላይም በግልፅ እንደ አንድ ምክረሃሳብ የተቀመጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፍትዊ ሸግግር ሂደት ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል፡፡ የህግ ማእቀፍ ተበጅቶለት በብሄራዊ ደረጃ ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል የሚል ምክረሃሳብ ነበር፡፡ ስለዚህ ይሄ ሃሳብ በስምምነቱ ተካቶ መንግስት እየሰራበት መሆኑ አንዱ የምክረሃሳባችን ተፈፃሚነት በዚህ ነው የሚለካው፡፡ እንግዲህ ፍትሃዊ ሽግግር ስንል አራት ነገሮችን ይይዛል፡፡ አንደኛው ተጎጂዎች መካሻ ማግኘት ሁለተኛ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ተካሂዶባቸው ክስ ተመስርቶባቸው አጥፊዎች በህጉ በተቀመጠው መሰረት የሚቀጡበት ሁኔታ ማስቀመጥ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ እውነትን ማውጣት ነው፡፡ ያ ሁኔታ የተፈፀመበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን እውነት በማውጣት ስምምነት ላይ መድረስ የውይይት መድረኮች በማድረግ ተጎጂዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ወይም ግጭቱን ያስነሳው አካል እውነታው ላይ ስምምነት መድረስ መቻል፡፡ አራተኛው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ተመልሶ እንዳይፈፀም አስፈላጊውን የፖሊሲ የተቋም ግንባታ የሚሰራበት ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም ብዙ ስራዎች የሚጠይቅ ብዙ ኮምፖነንቶች ያሉት አንዱ ከአንዱ ጋር በእኩልነት እንደ አንድ ሰፊ ፓኬጅ ተይዞ መከወን ያለበት ነው፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ በቅርቡ መንግስት ያወጣው ዶኩመንት አለ፡፡ እንዴት መከናወን ይችላል በሚል ውይይት እየተደረገበት የረገኛል፡፡ ተቋማችንም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት ፍትሃዊ ሽግግር በሚመለከት ሂደቱ በአገራችን ተሞክሮ አለ ወይስ ከውጭ ነው የሚናመጣው? የሚለውን ማህበረሰቡን በማወያየት እየተሰራ ያለ ስራ አለ፡፡ ይሄንን በአገር ደረጃ በማስቀጠል ፍትሃዊ ሽግግሩ በምን ዓይነት ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት በመለየት ለመንግስት ምክረሃሳብ ሆኖ እንዲያገለግል ፖሊሲ ወይም ስትራቴጂ በሚያወጣበት ግዜ እነዚህ ድምፆች እንዚህ ሃሳቦች አካቶ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ፡ – የኢሰመኮ ባለፉት ዓመታት ስራውን በገለልተኝነትና በውጤታማነት እንዳያከናውን ምን ተግዳራቶች አሉበት?
ራኬብ፡- ኮሚሽኑ እንደ ራዕይ አድርጎ የቀረፀው ሰብአዊ መብት ማክበር ባህል ሆኖ ማየት ነው፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ ህብረተሰባችን የሰብአዊ መብት እሴቶችን ማወቅ፣ መረዳት፣ እና መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይሄ ትልቅ ስራ ነው፡፡ የሰብአዊ መብቶችን ማስፋፋት፣ ማስተማር ባለግዴታዎች ግዴታቸውን ሃላፊነታቸውን አውቀው በዚያ መሰረት መተግበር እንዲችሉ የአቅም ግንባታ መስጠት መተግበር እንዲሁም ደግሞ ሰብአዊ መብቶች ይጣሱባቸዋል ተብለው ከሚወሰዱት እንደ ፖሊስ ጣቢያ፣ ማረሚያ፣ ተፈናቃዮች ያሉባቸው አካባቢዎች፣ እና ትምህርት ቤቶች በሙሉ ክትትል እያደረግን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ እርምጃ እንዲወሰድ በሚናደርግበት ግዜ የተቋሙን ሃላፊነትና ተግባር ባለመረዳት አንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደ አንድ ተግዳሮት የሚያጋጥመን ቦታዎችን እንዳንጎበኝና አንዳንድ ሰዎችን እንዳናነጋግር ክልከላዎች ይገጥሙናል፡፡ እሱን በሂደት እያስረዳን የበላይ ሃላፊዎችን እያነጋገርን ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እያደረግን ቢሆንም አሁንም በተወሰነ መልኩ ተግዳሮት የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌላው ምርመራ አድርገን ምከረሃሳብ ከሰጠን በህዋላ እንዲፈፀም ማድረግ ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጥሪ የሚናደርገው አስፈፃሚው አካልም ሆነ ህብረተሰቡ የኮሚሽኑ ሃላፊነትና ስልጣን ተረድቶ ስራዎቻችን በሚናከናውንበት ግዜ ሁኔታዎች እንዲያመቻችሉን ምክረሃሳብ በሚናወጣበት ግዜም ዋናው ዓላማም ሆነ መነሻው በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ ማድረግ ስለሆነ የማንንም ወገንተኛ ሆነን ሳይሆን ወገንተኛ ከሆንም የሰብአዊ መብት ጥሰት ለደረሰባቸው ወገኖች ስለሆነ ያንን እንደ አስፈላጊነቱ መፈፀም የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር እና ሁሉም ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት መከበር ባህል ሆኖ ማየት እንዲንችል የሁላችንም ትብብር የሁሉም ተቆርቋሪነት ስለሚያስፈልግ ለሁሉም ህብረተሰብ የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ አስ