ለክልሉ ህዝብ የማይጠቅሙ ድርጊቶችን ለመፈጸም ግንባር ነን ብለው ነገር ግን ጥሻ ለጥሻ የሚሽሎከሎኩ በመካከላችን የበቀሉትን አረሞች በአማራ ህዝብ የውስጥ ትብብር እና ጥረት ተነቃቅለው ይወገዳሉ – አማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ

አማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ በፌስቡክ ገፁ ባስነበበው መልዕክት ለክልሉ ህዝብ የማይጠቅሙ ድርጊቶችን ለመፈጸም ግንባር ነን ብለው ነገር ግን ጥሻ ለጥሻ የሚሽሎከሎኩ በመካከላችን የበቀሉትን አረሞች በአማራ ህዝብ የውስጥ ትብብር እና ጥረት ተነቃቅለው ይወገዳሉ ሲል አስጠንቅቋል።

ፓርቲው ለክልሉ ህዝብ የማይጠቅሙ ያላቸውን አካላት በስም ባይጠቅስም ነገረ ግን “ከመካከላችን እያፈነገጡ ለአንድነታችን እንቅፋት የሚሆን ደባ የሚፈጽሙብንን ተላላኪ ባንዳዎች በአንድ ልብ ሆነን ልናወግዛቸው ይገባለ” ብሏል፡፡

ጥቂቶች የአማራ ህዝብ ካሳለፈው የጦርነት አውድ በአግባቡ ሳያገግም ስንጥር ምክንያቶችን እየፈለጉ ግንባር ፈጥረን ጥያቄዎቻችንን በአፈ ሙዝ እናስመልሳለን ሲሉ ዳግም እልቂት ለመፍጠር በጀ ብለዋል ያለው መግለጫው ከህግ በላይ ለመሆን እና የአማራን ህዝብ ሰቆቃ ለማራዘም ሰላማዊ ትግልን ወደ ጎን ገፍተው አውዳሚ መንገድን የሚከተሉ ግንባር ነን ባዮች አደብ በማስገዛት እና ዳግም የአማራ ህዝብ አንድነት ጸር የማይሆኑበት ደረጃ ላይ በማድረስ ከፍታችንን የምናረጋግጥ ይሆናል ብሏል።

በአማራ ክልል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለህዝብ ሰላም እና ደህንነት መናጋት ብሎም ለኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች እደሚተዋሉ ጠቅሶ “እንደ ክልል ምላሽ ያላገኙ ጉዳዮች ሊሆኑ የሚችለው  በህግ እና ስርዓት ነውና ክልሉን ከሚያውኩ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች መቆጠብ ከዘላለማዊ የህሊና ጸጸት የሚገላግል ፍቱን መድሀኒት ነው” ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፏል።

የክልሉን ህዝብ እና መላው ኢትዮጵያዊያንን ከማሳዘን ውጭ የአማራ ህዝብን በማዋረድና አንገት በማስደፋት የሚፈጠር አንዳች ነገር አይኖርም ያለው የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችንም ሆነ በመካከል የሚያጋጥሙ ስንጥቆችን በክልሉ የውስጥ አቅም እንፈታቸዋለን በማለት ገልጿል።

በአስከፊው የሰሜኑ ጦርነት ከልክ በላይ ሲማቅቅ የባጀውን መላውን የአማራ ክልል ህዝብ ቁስል በማከም ከሁለንተናዊ ህመሙ እንዲያገግም ማድረግ እና ርቆት ከቆየው ክልላዊ ልማት ጋር በማገናኘት የአማራ ህዝብን አንድነትና ትንሳዔ ማረጋገጥ አለብን ሲልም አክሏል፡፡

ፓርቲው በመልዕክቱ ለአፍታም ቢሆን ተሳስተን አፈሙዝን ለማስቀደም መሞከር የለብንም ብሎ ይልቁንም ለአማራ ህዝብ አንድነት የሚበጀው ወንድማማችነትን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እና ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት በጽኑ አለት ላይ መመስረት ነው ብሏል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

ኮሚቴው በሚኖረው ቆይታ  በሀገራዊ እንዲሁም በፓርቲያዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎችንና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.