ዜና: የጥቁር አንበሳ የጤና ባለሙዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ሊያደርጉት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በፀጥታ ሀይሎች ተከለከለ

ማህሌት ፋሲል 

አዲስ አበባ መጋቢት 21 /2014 – የጥቁር አንበሳ የጤና ባለሙዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች አስተዳደራዊ ችግሮችን በመቃወም ዛሬ ጠዋት ፋና ቴሌቭዥን  ጣቢያ በር ላይ ሊያደርጉት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በፀጥታ ሀይሎች ተከለከለ። የጤና ባለሙያዎቹ  ለአስተዳደሩ  በርካታ ጥያቄዎች ቢያቀርቡም መልስ የሚሰጣቸው አካል ባለማግኘታታቸው በሆስፒታሉ ከሚሰሩ ከተለያዩ ክፍል የወከሉዋቸው ወደ 100 በሚጠጉ ሰራተኞች ተቃውሞዋቸውን ለማሰማት ወደ ፋና ቴሌቭዥን ቢሄዱም በርከት ያለ የፀጥታ አካለት ቦታው ላይ በመድረስ ከቦታው በትነዋቸዋል።  ሰራተኞቹ ወደ ቅጥር ግቢው ከገቡ በኋላ የሆስፒታሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና አማካሪ በተገኙበት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። 

ከቀረቡት ትያቄዎች መካከልም በ2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ለተሰለፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የተጨማሪ አበል ክፍያ እንዲፈጸምላቸው  የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያስተላለፈውን  ውሳኔ ችላ በማለት የተከፈላቸው  64 በመቶ ብቻ መሆኑን እና ቀሪው 34 በመቶ እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መልስ እንዳላደኙ ያስረዱ ሲሆን  ለሶስት ወራት የሰሩትም የትርፍ ሰአት ክፍያ እንዳልተከፈላቸውም ተናግረዋል።  ቀጥለውም ታካሚዎች ላይ እየደረሰ ያለው አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

የህክምና ባለሙያዎቹ ስለታካሚዎች ችግር ጥያቄ ሲያነሱ “እኛ ታካሚዎችን እያከምን ወይንስ እያንገላታን ነው ያለነው? ሆስፒታሉ ምንም አይነት የህክምና ቁሳቁሶች እያቀረበ አይደለም። አንድ ታካሚ ህክምና ለማግኘት የህክምና ጓንት ካልያዘ እየተስተናገደ አይደለም።  ይባስ ብሎም ከክፍለ ሀገር ድረስ የአልጋ ቀጠሮ ደርሷቸው የሚመጡ ታካሚዎች ከ15 ቀን እስከ አንድ ወር ጊዜ አልጋ ይዘው ከቆዩ በኋላ መድሀኒት የለም ተመልሳችሁ ኑ ይባላሉ።  ምን ያህል ታካሚ እየተሰቃየ እንደሆነ እናንተ አታዩም” ያሉ ሲሆን ሆስፒታሉ ማቅረብ ያቃተውን የህክምና ጓንት ከሆስፒታሉ ፊት ለፊት ያሉ ትንንሽ ሱቆች  አንዱን በ40 እና በ50 ብር ለታካሚው እየሸጡ መሆናቸውን እና  ከፍተኛ የመድሀኒት እጥረት መኖሩን አመልክተው  ለአመራሮቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

የሰራተኞቹን ጥያቄ ለመመለስ በቦታው የተገኙት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳሬክተር ዶ/ር አንዱአለም ደነቀ እና ምክትላቸው ዶ/ር ማቲያስ አቅርበዋልማካሪ በሆስፒታሉ ሰራተኖች ለተነሱት ጥያቄዎች  መልስ ሰጥተዋል። ሜዲካል ዳሬክተሩ ዶ/ር አንዱአለም ” የኮቪድ ክፍያ ቃል ሲገባም  ሆነ  66 በመቶ ክፍያ ሲፈፀም በወቅቱ  እኔ በቦታው አልነበርኩም። በአሁኑ ሰአት የኮቪድ ክፍያ አንድ ሳንቲም የለም። ይህንን ጥያቄያችሁን ለጤና ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተወካዮቻችሁ አማካይነት ጠይቁ”  በማለት የመለሱ ሲሆን  ሰራተኞቹ ለ3ወራት  ሰርተው ያልተከፈላቸውን የትርፍ ሰአት ክፍያን በተመለከተ  ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚሰጠው በጀት አነስተኛ መሆኑን አስረድተው ክፍያው የዘገየበት ምክንያት ከበጀት ማነስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነገር ግን አሁን ክፍያው እንዲደረግ ከሂሳብ ክፍል ጋር እየተነጋገሩ በመሆኑ  በትእግስት እንዲጠብቁ ተናግረዋል።  ታካሚዎችን በተመለከተ የህክምና ጓንት እና የተለያዩ መድሀኒቶችን  ከውጪ ይገዛሉ ለሚለው ጥያቄ  “እኛም እናውቃለን ግን የሚሰጠን በጀት ሳይጨምር የነሮ ግሽበቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። 300 ብር ይሸጥ የነበረው የህክምና ጓንት   በአሁኑ ሰአት 1000 ብር ገብቷል። ይህ የአገሪቷ ሁኔታ ነው እስኪስተካከል ወደ ፊትም ይገዛሉ” ብለዋል።

ሶስቱ የሆስፒታሉ ከፍተኛ አመራሮች ከሰራተኞች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በተወካዮቻቸው በኩል መልስ ለመስጠት እንዲሁም የተነሱትን ጥያቄዎች ወደ በላይ አካላት ወስደው የሚሰጣቸውን መልስ እንደሚያሳውቁ ተናግረው ስብስባውን በትነዋል። አስ  

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.