ዜና: የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲል ግጭት ለማቆም ወሰነ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15/2014 – የኢትዮጵያ መንግስት በ ትግራይ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ግጭት ለማቆም መወሰኑን  የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠውን የሰብአዊ ርዳታ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርም ተጠይቋል። 

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። በዚህም መሰረት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር እንዲሁም ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ የሚቀርብበትን ስርዓት የተሳለጠ እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማድረስ እንዲችሉ የአየር በረራ ተመቻችቷል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በአብአላ-መቀሌ የየብስ ትራንስፖርት መስመር በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መድረስ እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሰብዓዊ እርዳታን ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እየተጓዙ መሆኑ እየተስተዋለ ነው። በዚህም በትግራይ አጎራባች ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ከትግራይ ክልል የሚመጡ የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ዜጎችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳዩ ያለው በጎ ተግባር በህዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት እና የአንድነት መንፈስ የሚያሳይ ነው። መንግስት እነዚህ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታው ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ ባሉበት እንዲርሳቸው ቢደረግ እንግልታቸውን እንድሚቀንስ በጽኑ ያምናል።

በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቹን ችግር በአፋጣኝ የመፍታት ኃላፊነቱ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በመረዳት የአስቸኳይ የሰብዓዊ አቅርቦቶች ወደትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ መድረስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ ጥረቶች ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል።

በዚህም መሠረት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ እና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ከተለመደው የተለዩ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግስት ይህ ውሳኔ ከወጣበት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ አጋጣሚ መንግስት ዓለም ዓቀፉ የለጋሾች ማህበረሰብ እያቀረበ ያለውን ድጋፍ እና እርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ጥሪ ያቀርባል። የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በተሳለጠ ሁኔታ መድረስ እንዲችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል። ይህ የመንግስት ጥረት እና ቁርጠኝነት የሰብዓዊ ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ የሚኖረው ስኬት የሚረጋገጠው በሌላኛው ወገን የሚገኘው አካል በተመሳሳይ ለዚህ አላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት ልክ መሆኑን መንግስት ያምናል።

ይህ በመንግስት በኩል የተላለፈው ውሳኔ አላማው የአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በነጻነት ተጓጉዞ ለእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ለመድረስ እንዲችል ነው። በመሆኑም ለሰብኣዊነት ግጭት የማቆም ውሳኔ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም የጥቃት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ እና በጉልበት ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎችእንዲወጡ ይጠይቃል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህ ለሰብኣዊነት ግጭት የማቆም ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ በእጅጉ ሊያሻሽል እንደሚችል ብሎም በቀጣይ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.