አዲስአበባ፣ጥር 30/ 2015 ዓ.ም፡- የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ ።
በመከላከያ ሠራዊት መሰረት በአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር የሚገነባው የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ህንፃ በአራት መቶ ቀናት ዉስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን በዛሬዉ ዕለት የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ እና የስምምነት ፊርማ ተከናዉኗል፡፡ ይሁን እንጂ የሕንፃው ቦታ የት እንደሚሆን ግልጽ አይደለም፡፡
በዝግጅቱ ላይ በመገኘት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፤ ህንፃው ዘመናዊና ሁለገብ ሰራዊት ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች አንዱ አካል የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ በስራ ላይ እንዲውል አስፈላጊ የሆነ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ የገለፁት ኢታማዦር ሹሙ ህንፃው ሲጠናቀቅ ለሀገር ሀብት ለሰራዊታችን ደግሞ ኩራት ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ፤ ግንባታዉ ሶስት ዘመናዊ ባለአራት ፎቅ ህንፃን ጨምሮ የአንድ ሻለቃ ጦር መኖሪያን ያሟላ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘመናዊ የሆነው የህንፃ ኮምፕሌክስ ከዲዛይን ጀምሮ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረጠ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው ለአካባቢው ነዋሪዎችም ከፍተኛ የስራ ዕድል እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በተቋራጭነት የሚገነባው ሲሆን በመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ የዲዛይን ቁጥጥር መምሪያ ደግሞ እንደሚቆጣጠረው ታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ የመከላከያ ሚንስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ፤ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።
ምንጭ፣ የመከላከያ ሠራዊት።