ዜና: ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ህዝበ ዉሳኔ ከሶስት ሚሊዮን በላይ መራጮች ሊሳተፉ ይችላሉ አለ

የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ርእሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው የጸጥታ ሁኔታ ዝርዝር ዕቅድ አውጥተን እየሰራን ነው ሲሉ የክልሉን ዝግጁነት ገልፀዋል። ፎቶ: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም፡- በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች አና አምስት ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በመሆን አዲስ ክልል ለመፍጠር በሚያደርጉት ሕዘበ ውሳኔ ላይ በአጠቃላይ 3,106,585 (ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ስድስት ሺ አምስት መቶ ሰማንያ አምስት) ሰዎች በምርጫው ሊሳተፉ እንደሚችሉ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ህዝበ ዉሳኔዉን ለማስፈፀም ከተጠየቀው አጠቃላይ በጀት 541̄.3 ሚሊዮን ብር ዉስጥ 410.1 ሚሊዮን ብር ሊፈቀድ ችልዋል ሲል ምርጫ ቦርድ ሀሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቀዋል።

የምርጫ ምዝገባ የሚፈጀው ቀናት 15 መሆኑንም ጨምሮ አሳዉቋል።

በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚያካሄደው ሕዝበ ውሣኔ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለማድረግ ማቀዱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ይታወቃል። በዚህም መሰረት የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች ሕዝበ ውሳኔው ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

ህዝበ ዉሳኔዉ የአብላጫ መራጮችን ይሁንታ ካገኘ በኢትዮዽያ 12ኛዉን ክልል ለመመስረት ያስችላል።

ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የ6 ዞኖች (የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች) እና የ5 ልዩ ወረዳዎች(የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ) በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታን ተቀብሎ ከመረመረ በኃላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማስተላለፉ  ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ የጋራ ክልል የመመስረት ጥያቄው ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል የሕዝብን ይሁንታ ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ ገለልተኛ በሆነው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅና የሕዝብ ውሳኔው ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡

የህዝበ ውሳኔ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት ለህዝበ ውሳኔው 18 ሺህ 885 ሰዎች በአስፈፃሚነት እንደሚሰማሩ የገለፁት የቦርዱ የኦፕሬሽን አማካሪ አቶ ብሩክ ወንድወሰን አርባ ምንጭ ከተማ የህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ማዕከል እንደምትሆን ገልፀው የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.