አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 5/ 2015 ዓ.ም፡- በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል በተደረገው ውይይት “ሁሉም የኤርትራ ኃይሎች በአስቸኳይ ኢትዮጵያን ለቀው የመውጣት አስፈላጊነት ላይ” ተወያይተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ “የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አጣሪዎች ወደ ግጭት አካባቢዎች እንዲገቡ መጠየቋን” የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ገልጿል። ውይይቱ የተካሄደው ማክሰኞ ሲሆን በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ነው።
ብሊንከን ጥቅምት 23 2015 ዓ.ም በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል በደቡብ አፍሪካ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ዘላቂ ጦርነት የማቆም ስምምነት እንዲሁም በሁለቱ አካላት በኬንያ ናይሮቢ የተደረሰው የትግበራ ስምምነት አፈፃፀም የተከወኑ ተግባራትን አድንቀዋል።
“ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ አቅርቦትን ለማሻሻል እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ የወሰደውን ሂደት አድንቀዋል” ሲል የገለፀዉ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ፤ አክሎም “የስምምነቱ ትግበራ እንዲፋጠን እና ወደ ግጭት አካባቢዎች የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አጣሪዎች እንዲገቡ አሳስቧል” ብሏል።
የኤርትራ ኃይሎች መዉጣትን ጨምሮ የሰላም ስምምነቱ ትግበራ እንዲፋጠን ብሊንከን የጠየቁት የትግራይ ትጥቅ እንዲፈቱ የተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ በተጠናቀቀበት እንዲሁም ከትጥቅ መፍታቱ ጎን ለጎን ከትግራይ ይወጣሉ የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ “ንፁሃን ዜጎችን እየጨፈጨፉ ነው” የሚል ክስ በተደጋጋሚ እየቀረበ ባለበት ወቅት ነዉ።
ምንም እንኳን የኤርትራ ጦር የአማራ ልዩ ሃይል እና ታጣቂዎች በትግራይ በመኖራቸው የጸጥታ ችግር ቢኖርም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ 65 በመቶ የሚጠጋ የትግራይ ክልል ታጣቂ ሃይል ከጦር ግንባር ስፍራዎች ለቆ ወደ ተመደበበት ቦታ መስፈሩን የትግራይ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ መናገራቸዉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ከአለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ለትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቶችን በሶስት አቅጣጫ ማለትም በአማራ ክልል በጎንደር እና በኮምቦልቻ በኩል እንዲሁም በአፋር ክልል በሰመራ ኮሪደር እያቀረበ መሆኑን ገልጧል።
የሁለቱ ባላስልጣናትን ምክክር ተከትሎ የወጣው የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ መግለጫ በናይሮቢው ስምምነት መሰረት ከኤርትራ ወታደሮች ጋር ከትግራይ ይወጣሉ ስለተባሉት “ከመከላከያ ዉጭ የሆኑ ሃይሎች” ምንም ያለዉ ነገር የለም።
ብሊንከን “አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አጣሪዎች” ወደ ግጭት አካባቢዎች እንዲገቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን መንግስት ከዚህ ቀደም የአለም አቀፍ የመብት ባለሙያዎች በጦርነቱ ውስጥ የተፈጸሙትን ጥቃቶች እንዲመረምሩ የቀረቡ ጥሪዎችን ሲቃወም ቆይቷል።
በተኩስ ማቆም ስምምነቱ አንቀጽ 10 በንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ከኢፌዲሪ ህገ መንግስት እና ከአፍሪካ ህብረት የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ ጋር በሚስማማ መልኩ የተጠያቂነት፣ እውነትን ማረጋገጥ፣ ተጎጂዎችን የመካስ ፣ የእርቅና ማገገምን ያማከለ አጠቃላይ አገራዊ የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋል”። ይህም የፍትህ እና የተጠያቂነት አስፈላጊነትን በማቃለል ከመብት ድርጅቶች ትችት ቀርቦበት ነበር።
“አጋርነታችንን ማጠናከር”
ከስብሰባው በኋላ ጠ/ሚር ዐቢይ በትዊተር ገጻቸው ኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት በምታደርገው ጥረት ላይ አሜሪካ ላደረገችው አስተዋፅዖ እናመሰግነው ከብሊንከን ጋር ግልጽ እና ውጤታማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
“ለአስርተ አመታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ሆና ቆይታለች፤ አጋርነታችንን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ተወያይተናል” ሲሉ ጠ/ሚ አብይ ጨምረው ገልፀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንም ውይይቱ “የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት አንዲሁም አጋርነት አንደገና የማደስ እስፈላጊነት” ላይ አጽንኦት የሰጠ ነዉ ብለዋል።
“የአፍሪካ ህብረት የሰላም ስምምነቱ ክትትልና ማረጋገጫ ዘዴን ጨምሮ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ አንደሆነች” አሜሪካ በድጋሚ አቋሟን ገልፃለች። ብሊንከን በትዊተር ገፃቸው “የተኩስ ማቆም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ አስካሁን ለውን ሂደት አንዲሁም የፒሪቶርያውና የናይሮቢው ስምምነት በሁሉም አካላት በሙሉ አቅም ተግባራዊ ሲደረግ ኢትዮጵያን መልሶ የማገገም አውንታዊ ተጽአኖ እንዳለው” ከጠ/ሚ አብይ አሕመድ ጋር ተወያይተናል ብለዋል።አስ