ዜና፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) መስራች እና ከፍተኛ አመራሩ አቶ አንዷለም አራጌ መልቀቂያ አስገቡ

አቶ አንዷለም አራጌ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሩ አቶ አንዷለም አራጌ መልቀቂያ ማስገባታቸውን በማህበራዊ የትስስር ፌስቡክ ገጻቸው ይፋ ባደረጉት ደብዳቤ አስታወቁ።

ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ ድርሳን ላይ ከሰፈረው መከራዋ ሁሉ የከፋውን በምታስተናግድበት በዚህ ዘመን ፓርቲው የሚጠበቅበትን ከመወጣት ይልቅ ለገዢው ፓርቲ በማሸብሸብ የአገዛዝ ጡጫ እንዲፈረጥም ማድረጉ ለብዙዎች ፍች ያልተገኘለት ቅዠት ሆኖአል ሲሉ የፓርቲውን አካሄድ ተችተዋል።

ፓርቲው አሁን ያለበትን ሁኔታም ሲገልጹ ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ከስሁት መንገዱ ለመመለስ በማይችልበት መዳፍ ውስጥ መጨመቁ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የፓርቲውን ችግር ለመፍታት የሁኔታ ትንታኔ በመስራት ሳቀርብ ነበር ያሉት አቶ አንዷለም ለውጥ ሲመጣ አላየሁም ሲሉ አለመተግበሩን ጠቁመዋል። የፓርቲያችንን ቁመናና አሰላለፍ ከወዲሁ እናስተካክል የሚል ተማጽኖ ከማቅረብም ባለፈ በአባላት ፊት ቀርቤ ብሞግትም የሚገባውን ድጋፍ ባለማግኘቴ ውሳኔያቸውን በጸጋ ተቀብዬ በአባልነት መቀጠሌ ይታወቃል ሲሉ ከፓርቲው ከተለዩ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.