ዜና፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶችን የሚያስተላልፉ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃንን አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15/ 2015 ዓ.ም፡- ለሚከተሉት ሃይማኖት አገልግሎት እንዲጠቀሙበት የተፈቀደውን መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም የዜጎችን ሰላምና አብሮነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ኃላፊነት የጎደላቸው መልእክቶችን በሚያስተላልፉ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኋን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ትላንት ባወጣው መግለጫው እንዳስታወቀው የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ማኛውንም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም ሲያሠራጩ በተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሣሣት፣ የሌሎችን ሃይማኖት ወይም እምነት ማንኳሰስ፣ ወይም በሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ እንደሌለባቸው በሕገ መንግስቱ በግልፅ የተቀመጠ መሆኑን ገልጧል፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 70፣ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ በተደነገገው መሠረት በተለያዩ አማኞች መካከል መቃቃርንና ጥላቻን የሚፈጥሩ መልእክቶች መተላለፍ እንደሌለባቸው መስፈሩን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ባለሥልጣን መ/ቤቱ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ክትትል ክፍል ግኝች ከዜጎችና ከተቋማት የደረሱት  ቅሬታዎችና ጥቆማዎች እንዳመለከቱት፣ የተወሰኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚጠበቅባቸው ሕጋዊ፣ ማኅበራዊ እና ሞያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ መልእክቶችን እንደሚተላለፉባቸው ተስተውሏል ብሏል፡፡

እንደነዚህ ዓይነት የዜጎችን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ፣  ሁከትና ግጭት የሚጋብዙ እና በግለሰቦችና በማኅበረሰቦች ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሱ ንግግሮች በሚሰራጭባቸው የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ  ገልጧል፡፡

የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሃይማኖታዊ አስተምህሯቸውን ለተከታዮቻቸው ሲያስተምሩ የሌሎችን ሃይማኖትና እምነት አክብረው መሆን እንዳለበትም ባለስልጣኑ ጠቁሟል፡፡

ከተቋቋሙበት መርሕና ዓላማ በተቃረነ አኳኋን በተለያዩ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚፈጸሙ ሕጋዊና ሞያዊ የሥነ ምግባር ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ በጥብቅ ያሳሰበው ባለሥልጣኑ ህጉን በማያከብሩ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ በሕጉ መሠረት እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መግለጫዉ ከስሞኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሃይማኖትን ክብር የሚነካ፣ የአምልኮ ሥርዓትና እምነትን የሚያንቋሽሽ፣ ዘለፋና ሓሰተኛ ንግግር፣ አድርገዋል ባለቻቸው በወንጌላዊያን ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግ ለፌዴራል ፖሊስ አቤቱታ ማቅረቧን ተከትሎ ነው፡፡

ባለስኅጣኑ ከሰሞኑ በተወሰኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ላይ የቀረቡትን ቅሬታዎች ከሕግና ከሞያ ስነምግባር አንፃር መርምሮ እንአስፈላጊነቱ ውጤቱን ለፍትሕ አካላት እንሚያቀርብ አስታቋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.