ዜና፡ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ድርድር ካልሆነ ሽምግልና እንደማይቀበል አስታወቀ

አቶ ደሳለኝ ጣሰው፡ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ምንጭ፡ አሚኮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በዋግ ህምራ ዞን የሚንቀሳቀሰው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ድርድር ካልሆነ በስተቀር ሽምግልና እንደማይቀበል የንቅናቄው የውጭ ግንኙነት እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መምህር ባየ በሬ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁ።

በአከባቢው የተመደቡት ሊቀጳጳሱ በተገኙበት የአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎችና አመራሮች፣ የዋግ ህምራ ዞን አስተዳደር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የእኛም የአዴን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለሶስት ግዜያት ያክል ተገናኝተናል ያሉት የንቅናቄው ቃል አቀባይ በአማራ ክልል መንግስት እና በአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መካከል እስካሁን ያለው ነገር ሽምግልና የሚመስል ነው ብለዋል።

ሶስት ግዜ ተገናኝተናል፣ ሁለቱ ፍሬያማ ንግግር ያደረግንበት ነው ያሉት ቃልአቀባዩ ሶስተኛው ላይ ተገናኝተን ስንለያይ ውይይቱ ወደ ድርድር እንዲያድግ አሳይመንት ሰጥተናቸው ሂደዋል ብለዋል። ለምን ሽምግልናውን አልተቀበላችሁም ድርድሩን ለምን ፈለጋችሁ ብለን የተጠየቅናቸው ቃልአቀባዩ በኛ በኩል ያለው አቋም አንደኛ ሽምግልናው ሰላሙን በዘላቄታዊ መንገድ የመፍጠር እድሉ ዝቅተኛ ነው የሚል ነው ሲሉ ገልጸው ሁለተኛ እኛ እየታገልን ያለነው የራሳችን ምክንያቶች አሉን የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ እና የራሱን ክልል ለመመስረት የሚል ነው፤ ስለዚህ አሁን ያለው የሽምግልና ሂደት የአገውን ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ለማምጣት የሚበጅ ባለመሆኑ በኛ በኩል የድርድር መልክ ቢኖረው እና አደራዳሪዎች ተገኝተው ውይይት ተደርጎ በዶክመንት እና በፊርማ የሚያልቅ ከሆነ ዘላቂ ሰላም ስለሚያመጣ ለእኛም ለተነሳንለት አላማ ለማሳካት ይረዳል በሚል ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ሂደቱ እንደቀጠለ ነው፣ የተቋረጠ ነገር የለም ያሉን ባየ በሬ ይሄን አሳይመንት ይዘው ሂደው በድርድር መልክ ይመለሳሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፤ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ እነሱም የቤት ስራቸውን ሰርተው በድርድር መልክ እንደሚመለሱ ተስፋ እንዳረጋለን ብለዋል።    

በአማራ ክልል መንግስት እና በአዴን መካከል እየተካሄደ ስላለው ውይይት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዝዳን አቶ አላምረው ይርዳው የአማራ ክልል መንግስት “ሽምግልና በሚል ለማታለል ጥረት እያደረገ ይገኛል” ሲሉ ተችተው ከዚህ በፊት የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የቅማንት ኮሚቴ አባላት ላይ ተፈጸመ ያሉትን በአብነት አስቀምጠዋል።

የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የቅማንት ኮሚቴ አባላት የሆኑ ጫካ የገቡትን መከላከያ ውስጥ ያሉትን ጀነራሎች ጭምር በመጠቀም እንዲያባብሏቸው በማድረግ በአስራ አንድ ነጥቦች ስምምነት ደርሰናል በሚል የአከባቢው የገዳም ሃላፊ ጭምር እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲገቡ መደረጋቸውን ያወሱት አቶ አላምረው ሶስት ወራት ተሃድሶ ምናም እያሉ ካቆዯቸው በኋላ የክልሉ የጸጥታና ሰላም ሃላፊ ባለሁለት ነጥብ ስምምነት ጽፈው ፈርሙ እንዳሏቸው ገልጸዋል። ነጥቦቹም አንደኛ የቅማንት ጥያቄ አይደለም ህወሓት አዞን ነው ስንዋጋ የነበረው የሚል ሁለተኛው ደግሞ በአማራ መንግስት እና በቅማንት መካከል የተፈጠሩ ማንኛውም ችግሮች ሃላፊነት እንወስዳለን ብላችሁ ፈርሙ አሏቸው አንፈርምም አሉ፤ ሰብስበው አሰሯቸው ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል የሽምግልና አካሄድ የሃይማኖት ሰዎችን ይልኩና ተው ተው ተብሎ እንዲገቡ ይደረጋል ከዚያ በኋላ ግን የሚታመን መንግስት አይደለም ያሉት አቶ አላምረው በባህላችን ሽፍታ እንኳን እንደዚህ አያደርግም፤ ምህረት ከተሰጠ በኋላ እንዲህ አይደረግም፤ እነዚህን አስረው ነው እንግዲህ ቅማንትን በተመለከተ አንዳንዶቹን አስረናል አንዳንዶቹን ወደ ህግ እንዲቀርቡ አድርገናል የሚሉት ብለዋል።

በተመሳሳይ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄንም እንደዚሁ ማድረግ ነበር የፈለጉት ሲሉ ገልጸው በአከባቢው የተከበሩ አባት አሉ ጳጳስ ናቸው እሳቸውን እና ሌሎች ሽማግሌዎችን እየላኩ በዚህ መንገድ ጥያቄውን አደባብሰው እና ደባብቀው ለማስቀረት ነው የሚፈልጉት ሲሉ ኮንነዋል።

የክልሉ የጸጥታ ሃላፊ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በሰጡት ቃለምልልስ የአማራ ክልል መንግስት ሰላም እንደማይፈልግ ያሳየ ነው ያሉት አቶ አላምረው አሁንም የክልሉ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ንቀት የተሞላበት ነው ሲሉ ተችተዋል።

በሶስተኛ ወገን እንደራደር መባሉን አስመልክቶ የክልሉ የጸጥታ ሃላፊ ለቪኦኤ ሲናገሩ እንደሰማናቸው እነሱ እንደ ህወሓት በፌደራል ደረጃ ነው መታየት የሚፈልጉት ማለታቸው ንቀታቸውን ያሳያል ያሉት አቶ አላምረው የአገው ህዝብ ከትግራይ ህዝብ የሚያንስበት ምን ነገር የለም፤ የትግል ጥያቄ ደግሞ ሁለትም፣ ይሁን ሶስት መብትን ማስከበር ነው፤ እነሱ ሁልግዜ በንቀት እና በትእቢት ተወጥረው ነው አገር እያመሱ የሚኖሩት ሲሉ ኮንነዋል።

ስለዚህ ከቅማንት ተሞክሮ በመውሰድ የማይታመን መንግስት ስለሆነ የፌደራል መንግስትም ገብቶበት፣ ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት የአማራ ክልል መንግስት እና አዴን የመረጡት ሽማግሌ ባለበት እንደራደር የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን አቶ አላምረው በቦጎ አይን እንደሚያዩት አመላክተዋል።

የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የሚባለው ፓርቲ መስራቾች የአገው ብሔራዊ ሸንጎ የዋግ ህምራ ዞን ስራ አስፈጻሚዎች የነበሩ መሆናቸውን እና መስራቾቹ ግፉ ሲበዛባቸው ጠመንጃ አንስተው የትጥቅ ትግልን አማራጭ እንዲያደርጉ አቶ አላምረው ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸው  እኔም ይህ ነገር ከመሆኑ በፊት አዝማሚያውን ስላየሁኝ በወቅቱ ለነበሩት የብልጽግና የክልሉ ሃላፊዎች እንዲሁም ለክልሉ ፕሬዝዳንት ደውየ እባካችሁ እንነጋገር እባካችሁ እነዚህን ልጆች እየገፋችኋቸው ነው ብል የሚሰማኝ አጥቸ አሁን ያለንበት ደረጃ ተደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ የትጥቅ ትግል በማድረግ ለሚንቀሳቀሰው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የሰላም ጥሪ ማቅረቡን የተመለከተ ዘገባ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የአማርኛው ፕሮግራም አስደምጧል። የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ በዋግ ኽምራ ዞን በአበርገሌ እና በፃግብጂ አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ ለጠቀሱትና “አገው ሸንጎ” ሲሉ ለጠሩት ታጣቂ፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የክልሉ መንግሥት፥ የሀገር ሽማግሌዎችንና ከፍተኛ አመራሮችን በተደጋጋሚ በመላክ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.