ዜና፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቀጣይ ስምንት አጋማሽ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተገለጸ

ክሊንተን እና አብይ በዩኤስ አፍሪካ ስብሰባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/ 2015 ዓ.ም፡– የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቀጣይ ሳምንት አጋማሽ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ መስሪያ ቤታቸው አረጋገጠ። አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግስት እና ከትግራይ  ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ገልጸው መቀሌ ይሄዳሉ ተብሎ ግን እንደማይጠበቅ ጠቁመዋል።

ብሊንከን በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን እና የሽግግር ፍትህ ለማስፈን፣ እንዲሁም የጦርነት ማቆም ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተገልጿል። በተጨማሪም በሰብአዊ እርዳታ አሰጣጥ፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብአዊ መብቶች ላይ ለመወያየት ከሰብአዊ አጋሮች እና ከሲቪል ማህበረሰብ ተዋናዮች ጋርም እንደሚገናኙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ ያወጣው መረጃ አመላክቷል። ብሊንከን በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር  ሙሳ ፋቂ ማሃማት ጋር በመገናኘት በአህጉራዊና አለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ የጠቆመው መግለጫው በተጨማሪም በዩኤስ አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ስምምነት በተደረሱ ጉዳዮችም እንደሚመክሩ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ የአንቶኒ ብሊንከንን ጉብኝት በተመለከተ ለጋዜጠኞች በቴሌኮንፍራንስ በሰጡት ገለጻ ብሊንከን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁነው ከተሾሙ ጀምሮ የኢትዮጵያን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ይከታተሉት እንደነበር አስታውቀው በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል ብለዋል። ከኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም ሀገራቸው ጥረት ማድረጓን የጠቆሙት ሞሊ ፊ የብሊንከን ጉብኝት የተደረሰው ስምምነት እንዲጠናከር ለማስቻል የሚደረገው ጥረት አካል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኤርትራ እና የአማራ ክልል ሀይሎች በትግራይ መኖራቸውን በተመለከተ ያላቸው መረጃ ምን እንደሆነ የተጠየቁት ሞሊ ፊ ጉዳዩን አስመልክቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በሚገናኙበት ጊዜ በተደጋጋሚ ያነሱት መሆኑን ጠቁመው እስከማውቀው ድረስ እና የአፍሪካ ህብረት ክትትል ቡድን እንዳረጋገጠው በትግራይ የነበረው ጦርነት ቆሟል፤ በርካታ ቁጥር ያለው የኤርትራ ጦርም ከአከባቢው ለቋል፤  ይሁን እንጂ አሁንም ጉዳዩን የምንወያይበት ይሆናል ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.