ዜና፡ የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ወደ ክልሉ ለመመለስ ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1/2015 ዓ.ም፡- በዘንድሮ 2015 ዓ.ም ትምህርት  አመት የ12ኛ ክፍል ፈተና ለመፈተን በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው የነበሩ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ወደ ክልሉ መመለስ ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ እንዲቆዩ መደረጋቸውን መምህራኑ ለአዲስ ስታንዳረድ አስታወቁ።

“በአማራ ክልል ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ፤ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጠየቀው መሰረት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ህግ የማስከበር ስራ እተከናወነ” መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች እተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያም በርካታ መንገዶች የተዘጉ በመሆኑ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ከአማራ ክልል ወደ ተለያዩ ክልሎች የተላኩ ብርካታ መምህራን ፈተናውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ክልሉ መመለስ አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ባጋጠመ ግጭትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ ቀደም ብሎ ሲሰጥ የቆየውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ለመፈተን ወደ ተለያየ ዩኒቨርሲቲዎች ካቀኑ መምህራን አንዱ የሆኑት የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህሩ መምህር እንዳለማው ዋለ፣ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተመድበው ሲፈትኑ እንደነበር ገልፀው ከፈተና ኤጀንሲ አስተባባሪዎች ተደውሎላቸው በኤጀንሲው ግቢ በመገኘት ሪፖርት ማድረጋቸውን እና ወደ መጡበት ዩኒቨርስቲ መመለስ እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ በጊዜያዊነት የሚቆዩበት ማረፊያ እንደተዘጋጀላቸው ገልፀዋል።

መምህር እንዳለማው በትላንትናው እለት አዲስ አበባ የደረሱ መምህራን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ እንዲያርፉ መደረጋቸውን ገልጸው በዩኒቨርስቲው የተዘጋጀው ማረፊያ በሞምላቱ ሌሎች ማረፊያዎች እስኪዘጋጁ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል።  

ሌላኛው በአሶሳ ዩኒቨርስቲ በፈታኝነት ተመድበው ጨርሰው መመለሳቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ያስታወቁት የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አሳምሬ በበኩላቸው በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ወደ ክልሉ መምህራኑን መመለስ የሚችል ዩኒቨርስቲ አለመኖሩን ገልጸው የትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ባዘጋጀው ጊዜያዊ ማረፊያ ለመጠቀም መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

“በመንግስት የሚሰጠን አበል ከ420 ብር የማይበልጥ ነው፣ ከዚህም 40 በመቶ የሚሆነው ለመኝታ የሚታሰብ ነው” ሲሉ የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰሩ በአዲስ አበባ በዚህ የአበል ክፍያ ለመቆየት እጅግ አዳጋች ነው ብለዋል። በተጨማሪም በክልሉ ባለው ግጭት ሳቢያ የሐምሌ ወር ደመወዝ እንዳልገባላቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው ሲፈትኑ የነበሩ የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች መምህራንን የክልሉ ችግር እስኪፈታ በአዲስ አበባ ግዜያዊ ማረፊያ ተዘጋጅቶላቸው እዲያርፉ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው ሲሉ አስተባባሪዎቹ እንደገለጹላቸው መምህራኑ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ምን ያክል የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲ መምህራን በአዲስ አበባ በተዘጋጀላቸው ግዜያዊ ማረፊያ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም አስተያየት የሰጡን መምህራኑ በአጠቃላይ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ላይ የተሳተፉ አንድ ሺ የሚደርሱ መምህራን እንደነበሩ ከነዚህም በርካታዎቹ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በክልሉ በመከላከያ ሀይል እና ኢ-መደበኛ ኃይሎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈታኝነት ተመድበው የሄዱ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር የነበሩት ታደሰ አበበ ገብረሀና (ረ/ፕ/ር) እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባሎች መገደላቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል።

ትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪ ፣ ፋሲል እና ቴዎድሮስ በተባሉ ሶስት ካምፓሶች ላይ ሐምሌ 27 ባጋጠመ ችግር 16 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይፈተኑ ቀርተዋል ማለቱን፣ ተማሪዎቹ በቀጣይ በሚመቻች መርሐ-ግብር ይፈተናሉ መባሉን በዘገባችን ተካቷል። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ካጋጠመው ችግር ውጪ በአማራ ክልል በሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠው ፈተና በሰላም ነው የተጠናቀቀው ያለው ተቋሙ በአማራ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም የአውሮፕላን በረራ በተቋረጠባቸው አካባቢዎች ያሉ የፈተና አስፈጻሚዎች ሁኔታው እስከሚረጋጋ ድረስ ትንሽ ቀን መጠበቅ አለባቸው ሲል በወቅቱ አሳስቧል፡፡

በአማራ ክልል አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሓምሌ 28 በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞhራሲያዊ ሪፐብሊh ሕገ መንግሥት መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የጸና ይሆናል ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.