ዜና፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣን በመልቀቅ የመፍትሔ አካል ለመሆን አስበው እንደሆነ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም፡- ዛሬ መጋቢት 19 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡት ጥያቄ እያነጋገረ ይገኛል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ “እርስዎስ ሥልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔው አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አክለውም በሰብአዊነት ላይ በተፈፀሙ እንዲሁም የማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳትና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት? ሲሉ ጠቅላይ ሚንስቴሩን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን ይህንን ለየት ያለ ጥያቄ ከማቅረባቸው አስቀድመው “ጥያቄዬን ከማቅረቤ በፊት ስለጥያቄዬ ትንሽ ማለት እፈልጋለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ምክር ቤት እና በተለያዩ መድረኮች ስለእርስዎና ስለሚመሩት የአስፈፃሚ መንግስት ተጠየቅ ሲቀርብብዎ ለተጠየቁ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጠያቂዎችን የሚያጥላላ አስተያየት ሲያራምዱ፤ አለፍ ሲልም ተጠየቅ የቀረበብዎት የወጡበት ብሔርን በመጥላት እንደሆነ አድርገው ምላሽ መስጠትዎ የቅርብ ትዝታ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ጠያቄዬን የማቀርብልዎ ጥያቄ ራስዎንና መንግስትዎን የሚመለከት እንጂ ሌላ ማንንም የማይመለከት መሆኑን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። እኔም ጥያቄውን የማቀርብልዎት በብሔር አይደለም። ምላሽ ሲሰጡም የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ የተሼረበ ሴራ ነው የሚል እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ጥያቄዬ የሚከተለው ነው” በማለት ወደ ጥያቄያቸው አምረተዋል።

“የዜጎችን ደህንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ዝቅተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ፤ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ቤታቸው ይፈርሳል፣ ንብረታቸው ይወድማል። የሀገር ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ የጎረቤት ሀገራት ሰራዊቶች በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ወሰኖች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል። ይህ ቀደም ሲል፤ ከእኔ የቀደሙ የተከበሩ የምክር ቤት አባላትም በጥያቄ መልክ ያቀረቡት፣ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በሪፖርቱ ደጋግሞ፤ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ስለሚገደሉ ዜጎች፣ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ወንጀሎች፣ መፈናቀሎች፣ ግድያዎች፣ ቤት መፍረሶች በሪፖርቱ ያቀረበው ነው።”

“አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደህንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት ዋነኛ ስጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው እርሶ የሚመሩትን መንግስት ነው። እርሶ በአፍዎ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’ ቢሉንም፤ በተግባር ግን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በመንግስትዎ እየተናዱ ነው። የበርካታ ሀገራት መሪዎች መሰል ኃላፊነትን በወጉ ያለመወጣት ጉድለት ሲያሳዩ፤ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀው ስልጣናቸውን ሲለቁ ይታያል። በሀገራችንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተመሳሳይ ህዝባዊ ተጠየቅ ሲቀርብባቸው ስልጣን መልቀቃቸውን እናስታውሳለን። እርሶም ወደ ስልጣን የመጡት በዚህ ተጠየቅ ምክንያት ነው። እርስዎስ ስልጣንዎን በመልቀቅ የመፍትሔ አካል ለመሆን አላሰቡም ወይ? በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ እንዲሁም በማንነት ተኮር የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት እና የማንነት ማሳሳት ወንጀሎች ተጠያቂ ለመሆን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?”  ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስቴሩም ምላሽ ሲሰጡ ስልጣን ብትለቅ የሚለው ጥያቄ ጥሩ ጥያቄ ነው በማለት ገልፀው ቀጥለውም ጥሩ የሚሆነው በጋራ ስልጣን ብንለቅ ነበር ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምክኒያቱም የሁሉም ችግር ምንጭ እና ባለቤት እኔ ብቻ አይደለውም ማለት አልችልም ሃላፊነት ከወሰድንም በጋራ ቢሆን ጥሩ ይሆናል ብየ አስባለው” ሲሉ መልሰዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.