ዜና፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ስራ የለቀቀ ሃላፊ የለም ሲል አስተባበለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስራ ሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ዘኒው ሂዩማኒተርያን የተሰኘ ድረገጽ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል። የአለም የምግብ ፕሮግራም በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ትዊተር ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ ጉዳዩን አስተባብሏል። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተቋሙ የኢትዮጵያ ሃላፊዎች ለቀቁ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ ነው ሲል ገልጿል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የተቋሙ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውዲ ጂቢዳር እረፍት ላይ መሆናቸውን እና አሁንም የድርጅታችን ባልደረባ ናቸስ ሲል ገልጿል። የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተሮች ሁሉም በስራ ላይ ይገኛሉ ሲል የገለጸው የአለም የምግብ ፕሮግራም ስራ መልቀቃቸው የተነገረው ምክትል ዳይሬክተሩ ጀኒፈር ቢቶንዲ ስራቸውን እያከናወኑ በተቋሙ ይገኛሉ ሲል ጠቁሟል። የለቀቀ ማንም ከፍተኛ ባለስልጣን የለኝም ሲል አስተባብሏል።

የአለም የምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለማጣራት ውሳጣዊ ምርመራ ለማካሄድ በሚል በትግራይ የሚያካሂደውን እርዳታ ማቋረጡ ይታወቃል። የምርምራው ውጤት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ተጠቁሟል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የሆኑት ማይክ ሃመር ከመሩት ሉዑክ ጋር ባደረጉት ምክክር በእርዳታ እህል አቅርቦቱ መቋረጥ ዙሪያ መወያየታቸውን በማህበራዊ ሚድያ ትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አቶ ጌታቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ለማይክ ሀመር እና ሉዑካቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላልተገባ አላማ በስርቆት ውሏል ስለተባለው የእርዳታ እህል በምርመራ ያገኘውን ውጤት እንደገለጹላቸው እና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ጥፋተኞቹን በቅርቡ ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል። የአሜሪካ መንግስት የተቋረጠውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት በአፋጣኝ እንዲያስጀምር መጠየቃቸውንም አካተዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.