አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28/ 2015 ዓ.ም፡- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቋቋመው የካቢኔ አባላት ውስጥ ሁለት አባላቱን ያካተተው ብቸኛው ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ “የፍትሃዊነት እና አሳታፊነቱ ላይ ያሰማው ተቃውሞ እንደተጠበቀ ሆኖ ገብቶ መታገልን እንደ አማራጭነት” መወሰዱን አስታወቀ፡፡
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከቋቋመው ካቢኔ መካከል ሁለት የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ አመራሮች የተካተቱ ሲሆን አቶ ሞገስ ገብረእግዚአብሄር የውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም አቶ ታደለ መንግስቱ ደግሞ የትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሁነው ተሹመዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲው ባይቶና ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ፀጋዘአብ ካህሱ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት የፓርቲያቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመጋቢት 1 ቀን እስከ 5 2015 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ሁለቱ አመራሮቹ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሰሩ መወሰኑን አስታውቀዋል። በአካሄዱ ላይ ማለትም “የፍትሃፊነት እና አሳታፊነቱ ላይ” ያለን ተቃውሞ እንደተጠበቀ ሆኖ ገብቶ መታገልን እንደ አማራጭነት መወሰዱን እና መወሰኑን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።
በጊዚያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ፓርቲውን የወከሉት ሁለቱ አባላቱ ከባይቶና እውቅና ውጪ ነው የተካተቱት በሚል የተጋራው መረጃ ከድርጅቱ የተሰናበተ ግለሰብ ቁጥጥር ስር በሆነ የፌስቡክ ገፅ የተለጠፈ መሆኑንና ከድርጅቱ እውቅና ውጭ ነው ሲሉ ዶ/ር ፀጋዘአብ ለአዲስ ስታነዳርድ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያለኝ ሊቀመንበር እኔ ነኝ ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ የገለፁት አቶ ኪዳነ አመነ የባይቶና ፓርቲ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተካተተ ምንም አባልም ሆነ አመራር የለንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አቶ ኪዳነ አመነ ባይቶና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከመነሻው ጥያቄ ሲነሳበት የነበር ነው፣ ይህንንም በወቅቱ ከሌሎች በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በይፋ አስታውቀን ነበር ሲሉ ገልፀው ምንም ባልተቀየረበት ሁኔታ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚካተት ተወካይ ልንመድብ የምንችልበት እድል የለም ብለዋል፡፡
በዶ/ር ፀጋዘአብ የሚመራው ባይቶና ምንም እውቅና የሌለው ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ አክለውም ከፓርቲው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከምርጫ ቦርድ ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል፡፡
በአቶ ጌታቸው ረዳ የተዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከባይቶና ፓርቲ ከተውጣጡ አባላት ያሉት ሲሆን ከካቢኔው 51 በመቶው የተያዘው በህወሓት መሆኑ ተገልጿል። ቀሪው 49 በመቶ ደግሞ ለትግራይ ታጣቂ ኃይሎች፣ ለትግራይ ምሁራን እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች መሰጠቱ ይታወቃል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጀነራሎ የነበሩት ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የምክትል ፕሬዝደንትነት ቦታን መያዛቸውም ተገልጿል። ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሰላም እና የጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኋላፊ ተደርገው መሾማቸው የተገለጸ ሲሆን ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከል አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኋላፊ ሆነው ተሹመዋል።
የትግራይ ታጣቂ ሀይሎችን ሲመሩ ከነበሩ ጀነራሎች ውስጥ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ፣ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ ኪሮስ የማህበራዊ ጉዳይ እና መልሶ ማቋቋም ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም ብርጋዴል ጀነራል ተክላይ አሸብር የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ካቢኔ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ተደርገው መሾማቸው ታውቋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከነባሩ አስተዳደር ከዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ስልጣን ትላንት መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. መረከቡን መዘገባችን ይታወሳል። በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ለአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር መልካም ሥራ ተመኝተው፣ የትግራይ ሕዝብ ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ጎን እንደሚቆም ገልፀው ሥራውን እንደምትሠሩት እርግጠኛ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል:: አዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል በጋራ ይሰራል ተብሏል። በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይን ህዝብ ህልውናና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት ሁሉንም የትግራይ ሃብቶች እንደሚጠቀም መናገራቸውም ተካቷል። አስ