አዲስ አበባ መጋቢት 16/2014 – የትግራይ ክልል ጦርነቱ በአስቸኳይ ለማቆም ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጽ መሬት ላይ ያለውን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ ተቀባይነት ባለው ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ የሚገባ ከሆነ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል ።
የትግራይ ክልል በትላንትናው እለት የፌዴራል መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ተከትሎ ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ ምላሽ ሰጥቷል። “የትግራይ መንግስት ይህ የግጭቱ መቆም የተሳካ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል” ሲል የገለጸው መግለጫው፣ የፌደራል ባለሥልጣናት ያልተገደበ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ለመድረስ ተጨባጭ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስቧል።
የፌደራል መንግስት ትላንት አመሻሽ ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቹን ችግር በአፋጣኝ የመፍታት ኃላፊነቱ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በመረዳት የአስቸኳይ የሰብዓዊ አቅርቦቶች ወደ ትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ መድረስ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማሳካት የተቻለውን ሁሉ ጥረቶች ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
የትግራይ ክልል በበኩሉ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ፍላጎትና ዝግጁነት ገልጾ የሰብዓዊ ዕርዳታ በበቂ ሁኔታ መግባት እና ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም መሰረታዊ የቴሌኮሙኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎቶችን መልሶ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ሰብአዊ እርዳታን ፖለቲካዊ አውድ መስጠት ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳው የትግራይ መንግሥት ፣ “የትግራይ ህዝብና መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲል መግለጫውን አሳርጓል።
በትላንትናው እለት የፌደራል መንግስት በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች እርዳታ ፍለጋ ወደ አጎራባች አማራ ክልል እየተሰደዱ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታው ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ ባሉበት እንዲደርሳቸው ቢደረግ እንግልታቸውን እንደሚቀንስ ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል ። አክሎም የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች በአጎራባች ክልሎች ከያዙት አካባቢዎች እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል። የፌደራል መንግስት ይህ የእርቅ ስምምነት እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለመፍታት መንገድ እንደሚከፍት ያለውን ተስፋ ገልጿል።
ባለፈው አመት ግንቦት ወር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው) በአሸባሪነት ለመፈረጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ማጽደቁ ይታወሳል። የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም። አስ