ዜና፡ ሰሞኑን በተደረገው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ጥር 18/ 2015 ዓ.ም፡– በሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ተስጥቷል በተባለው ጉዳይ ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ ለማስተላለፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ዛሬ መጀመሩ ተገለጧል።

ምልዓተ ጉባዔው የተጠራው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት ጥሪ መሠረት ነው።

ትላንት አመሻሽ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ የጸሎት መርኃ ግብር በመንበረ ፓትሪያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም የተካሄደ ሲሆን ስነስርዓቱም በቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ተላልፏል። የጉባኤ የመክፈቻ ጸሎቱን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተጉባኤ የዕምነቱ ተከታዮች የሶስት ቀናት ጸሎት እንዲያካሂዱ አውጇል። የምልአተ ጉባኤው ለምን ያህል ቀን እንደሚቆይ የተባለ ነገር የለም። ጉባኤው ስለክስተቱ በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በኦሮምያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በሶዶ ዳጬ ወረዳ በወሊሶ ከተማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና ውጭ ተፈጽሟል የተባለውን የ26 ጳጳሳት ሹመት የሰጡት ብጹዕ በአቡነ ሳዊሮስ መሆናቸው ይታወቃል።

በዓለ ሲመቱ ከተከናወነ በኋላ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሳዊሮስ በሰጡት መግለጫ ሲመቱን ለመፈጸም ያበቋቸውን አስገዳጅ ሁኔታዎች ዘርዝረዋል። በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸው ዘንድ አከባቢያቸውን የሚያውቁ እንዲሁም ቋቋቸውን የሚናገሩ አገልጋዮች ሊኖራት እንደሚገባ አመላክተው ይህ ባለመደረጉ ቤተክርትሲያኗ በተለይም በኦሮምያ እና ደቡብ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞቿን አጥታለች ብለዋል።

አቡነ ሳዊሮስ አክለውም 85በመቶ የሚሆነው የሲኖዶሱ አባላት ከአንድ አከባቢ የመጡ መሆናቸውን በመጥቀስ የቤተክርስቲያኗን የብሔር ስብጥር የማያንጸባርቅ ነው ሲሉ ተችተዋል።

በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሳዊሮስ በተደረገው ሲመት ከተሾሙት መካከል አባ ፀጋዘአብ አዱኛ የተባሉ አባት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ይቅርታ መጠየቃቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙሃን አሰራጭተዋል።

በሌላ በኩል በቤተክርስቲያኗ አከባቢ ጥበቃ ላይ ተሰማርተው የነበሩ የፖሊስ አባላት መነሳታቸውን  የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ አብርሃም ከትላንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። የፌደራል መንግስቱም ይሁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ይፋዊ መግለጫ የለም።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.