አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም፡- የአፍሪካ ህብረት የክትትል፣ ማረጋገጥ እና የተልዕኮ የማስከበር ሰንቆ የሚንቀሳቀሰው ኬሚቴ ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ የኤርትራ ሰራዊት እንቅፋት እየፈጠረበት መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።
አቶ ጌታቸው ይህንን የገለጹት ትላንት ግንቦት 11 ቀን 2015 የህብረቱን ኮሚቴ የሰላም ስምምነቱ አተገባበርን አስመልክቶ ከተላያዩ ሀገራት የተወከሉ የወታደራዊ አታሼዎች ጋር በመቀሌ ከተማ በተወያዩበት ወቅት ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በክልሉ ወረራ የፈጸሙ ሀይሎች በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲፈጥር ጥሪ አቅርበዋል። ወራሪ ሀይሎች ከትግራይ መሬት ሙሉ ለሙሉ ለቀው እንዲወጡ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የትግራይ ክልል መንግስት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የሚጠበቅበትን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻል አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁለቱም ሀይሎች በስምምነቱ የሚጠበቅባቸውን በፍጥነት እንዲፈጽሙ የሚጠበቅበትን ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
የህብረቱ የክትትል ኮሚቴው የበላይ ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ስቴፈን ራዲና የትግራይ ሰራዊት እስካሁን በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ከባድ መሳሪያዎቹን ማስረከቡን ገልጸዋል። በቀጣይ ሰኔ ወር ኮሚቴው በምዕራብ እና ደቡባዊ ትግራይ በመጓዝ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ ያሉ ሀይሎች መኖራቸውን እና አለመኖራቸውን እንደሚያረጋግጥ ጠቁመዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ የወደሙ የትግራይ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካ ህብረት እንደ አህጉሩ ተቋም አለም አቀፉ ማህበረሰብ የበኩሉን እንዲወጣ በአፍሪካ ህብረት የግጭት ማስወገድ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኣልሓጂ ሳርጆህ ባህ ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ህብረት በትግራዩ ጦርነት ግፍ የተፈጸመባቸው ዜጎች ፍትህ ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም ደግሞ እንደሀገር አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሌላ ዜና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቀጣይ ሶስት ወራት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ፣ በትምህርትና ጤና እንዲሁም በግብርና ዙሪያ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ አስታውቀዋል።
በትግራይ ከሚገኙ የተላያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ባካሄዱት ውይይት ወቅት አቶ ጌታቸው በተለያዩ ርዕሶች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ በክልሉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ በተለያዩ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶች በተደራጀ መልኩ እንዲሰጡ ማስቻል፣ የክልሉ ገበሬዎች የግብርና ግብአቶችን እንዲያገኙ ማስቻል ዋና ትኩረቱ አድርጎ እንደሚሰራ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ህዝቡን እያንገፈገፈው የሚገኘው የፍትህ እና የጸጥታ እጦትን ለመቅረፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። የክልሉ ህዝብ አንደነቱን አጠናክሮ ክልሉን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንዲረባረብ ጥሪ ማቅረባቸውን ከትግራይ ቴሌቪዥን እና ድምጽ ወያነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡