አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሃሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ምክር ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ባሰፈረው መረጃ አስታውቋል።
የሚንስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን፣ 2ዐ15 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለምክር ቤቱ አባላት ማቅረባቸውን የጠቆመው የምክር ቤቱ መረጃ ዋና ተጠሪው የአዋጁን አስፈላጊነት ማብራራታቸውን እና በማብራሪያቸውም በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት መፈጸሙንና የተፈጠረውን አለመረጋጋት በመደበኛው የህግ ሥነ ሥርዓት ለማስከበርና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ ይህም የክልሉን መንግስታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ እና የህዝቦችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል ብሏል።
ማብራሪያውን ተከትሎ በቀረበው ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ አስተያየቶች መስጠታቸውን እና ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን አመላክቶ በተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ዙሪያም በፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ የህዝብን ሠላም፣ የሃገርን ደህንነት እና ህግና ሥርዓትን ለማስከበር በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአዋጅ ቁጥር 1299/2015 በ12 ድምፅ ተአቅቦ በ16 ታቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ የመርማሪ ቦርድ አባላትን ሹመት በ1 ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ አባላት፡-
ሰብሳቢ የተከበሩ አዝመራው አንዴሞ
የተከበሩ ነጃት ግርማ ዶ/ር ምክትል ሰብሳቢ
የተከበሩ አቶ ሣዲቅ አደም አባል
የተከበሩ አቶ መስፍን እርካቤ አባል
የተከበሩ ዶ/ር አብርሃም በርታ አባል
ወ/ሮ ፍሬህይወት ተሾመ አባል
አቶ ወንድሙ ግዛው አባል በመሆን ተሰይመዋል፤ የቦርዱ አባላት በጉባዔው ፊት ቃለ ማህላ ፈጽመዋል፡፡ አስ