ዜና፡ ክርስቲያን ታደለ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአብን ላይ ተገቢ ማጣራት እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፤ ለአብን መዋቅሮች፣ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተገዢ እንዲሆኑ አሳሰቡ

ክርስቲያን ታደለ: የኢትዮጵያ ህዝብ እንደራሴ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ማዕካላዊ ኮሚቴ አባል። ፎቶ ፓርላማ

አዲስ አበባ፣ጳጉሜ 1፣ 2014 ዓ.ም፦ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደራሴ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ማዕካላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ክርስቲያን ታደለ ዛሬ ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ዓም በግል ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለአብን መዋቅሮች፣ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ደብዳቤ መፃፋቸውን አስታወቁ

እርሳቸው እንዳሉት “አብን እሁድ ነሐሴ 29/2014 ዓ/ም የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ምልዓተ ጉባዔው ባለመሟላቱ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል። እውነታው ይኼ ሆኖ እያለ ባልተካሄደ ስብሰባ፣ ውይይት ባልተደረገበት አጀንዳና ተገቢ ፖለቲካዊ ምክክር ተደርጎ ባልተላለፈ ውሳኔ፤ ስብሰባ እንደተጠራ፣ አጀንዳ ተዘርግቶ ውይይት እንደተካሄደና ውሳኔዎች እንደተላለፉ ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ የስነስርዓት ጥያቄዎች የሚቀርቡበበት፣ ድርጅታዊ አሰራርንና መርኅን የጣሰ እንዲሁም ከዴሞክራሲ ልምምድ ያፈነገጠ የነውር ሥራ ነው። የስንስርዓታዊ ጉዳዮች መሟላት ስብሰባው ከመካሄዱና በስብሰባው ከሚወሰነው ውሳኔ እኩል ወይንም የበለጠ አስፈላጊ በመሆኑ ባልተሟላ ምልዓተ ጉባዔ ስብሰባዎች አይካሄዱም” ብለዋል።

አቶ ክርስቲያን አክለውም “ለውጥ ፈር በሆኑ ጥቂት የአብን ከፍተኛ አመራሮች እየተደረገ ያለው ሁኔታ ግን ለንቅናቄው አባላትና አመራሮች ብቻ ሳይሆንም ለስርዓት ግንባታም ደንታ የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ሰኞ ነሐሴ 30/2014 የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አድርገን ውሳኔዎችን አሳልፈናል ይበሉ እንጂ የሰኞ ስብሰባ ስለመኖሩ የትኛው የድርጅቱ አካል፣ መቼና በምን መንገድ ጥሪ አስተላለፈ? ጥሪውስ ለሁሉም የማዕከላዊ አባላት እኩል ተላልፎላቸው ነበር ወይ? የድጋሚ ስብሰባ ቀኑ ሲወሰን ከስብሰባ ቦታው ርቀው የሚገኙ አባላትን የመጓጓዣ ቀናት ታሳቢ ያደረገ ነበረ ወይ? ወዘተረፈ ቀላል ግን መሰረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ተጨባጭ ነገር ማቅረብ አይቻላቸውም” ሲሉ ጥያቄያቸውን አስረግጠው ገልፀዋል።

የህዝብ እንደራሴው ባስተላለፉት መልዕክትም “ባለፈው እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ማኅተም ስለያዙ ብቻ የንቅናቄው የሥራ አስፈፃሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ያልመከረባቸውንና ያላፀደቃቸውን የኦዲት ሪፖርት እና የሪፎርም ጉባዔ (የደንብ ማሻሻያና የአመራር አመላለመል እንዲሁም አወቃቀርን ጨምሮ) ውይይት ተካሂዶባቸው የጸደቁ በማስመሰል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የደብዳቤ ልውውጦች ማድረጋቸውን ስለታዘብን፤ጉዳዩ የወንጀል ተጠያቂነትን ጭምር የሚያስከትል ጉዳይ ያለው ስለሆነ ይህንንም የሚመለከታቸው ተቋማት በተለይም የንቅናቄው በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች፣ አመራሮችና አባላት በልዩ ልዩ አማራጮች አሳውቀናል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔው የተወሰነበት ቃለጉባዔ ይምጣልኝ የሚል ደብዳቤ ስለፃፈ፤ የቦርዱን ጥያቄ አሰነባብቶና ቀባብቶ ምላሽ ለመስጠት በሚል ከስነስርዓት ውጭ ስብሰባ ተደርጎ፥ ውሳኔ እንደተላለፈ መግለጫ ማውጣት፤ በተደጋጋሚ ጊዜ የተፈፀመ ነውር እና የምርጫ ቦርድን በተሳሳተ ደብዳቤ የተሳሳተ ውሳኔና ግንዛቤ ላይ እንዲደርስ የሚደረግ የወንጀል ተግባር ተደርጎ የሚቆጠር ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም “መሰል ስህተቶችን ነቅሰን ጉዳዩ ለሚመለከተው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገብተናል። ቦርዱ ተገቢውን ማጣራትና ምርመራ አድርጎ ተገቢ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስም እምነት አለን። በተለይ ከኦዲት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከንቅናቄው አመራሮች ጭምር ይመርመርልን ጥያቄ የቀረበበት በመሆኑ እና የምርጫ ቦርድም መሰል ጥርጣሬዎችና ጥያቄዎች ሲቀርቡለት የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን ልዩ ኦዲት እንዲሰራለት የመጠየቅ መብት ስላለው፤ ይኽንኑ እንዲያደርግ ደግመን ማስታወስ እንፈልጋለን” ብለዋል።

መስተመጨረሻም የተከበሩ ክርስቲያን “መላው የአብን መዋቅሮች፣ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ንቅናቄያችን የሚያደርገው የለውጥ እንቅስቃሴ ለግላዊ ጥቅማቸው ሲሉ ከገዥው ፓርቲ ጋር በተጣበቁ ጥቂት ግለሰቦች መታገቱን በውል በመረዳት፤ ፓርቲው የተሟላ ሪፎርም አድርጎ መላው ሕዝባችን የሰጠውን አደራ እንዲወጣ በተገቢው ሁኔታ ብርቱ ትግል ታደርጉ ዘንድ መልእክቴን አስተላልፋለሁ” ሲሉ አስታውቀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.