አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5/2015 ዓ.ም፡– በኬንያ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በጸጥታ ችግር ሳቢያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የነበረውን ድንበር ዝውውር ለማስጀመር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። የፕሮጀክቱ መጀመር በሶስቱ ሀገራት መካከል ያለውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሻሻል ያደርጋል ሲሉ በኬንያ ማንዴራ ከተማ ፕሮጀክቱ በይፋ ሲጀመር ንግግር ያደረጉት የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ገልጸዋል። በአከባቢው በጦርነት ሳቢያ የመሰረተ ልማት ግንባታ ቆሞ እንደነበር የጠቆሙት ምክትል ፕሬዝዳንቱ የመሳሪያ ድምጾችን ጸጥ በማሰኘት ከኢንደስትሪ የሚወጡ ድምጾች ከፍ ብለው እንዲሰሙ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ መናገራቸውን አመላክተዋል። በአከባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ብልጽግና ማስፈን ይገባናል ማለታቸውም ታውቋል።
በዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ፈንድ አማካኝነት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በሀገራቱ የድንበር አከባቢ የሚስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ በማስወገድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ነው ተብሏል። ፕሮጀክቱ የተሰጠው ስያሜም በሶማሊኛ ቋንቋ “Deris Wanaag” ሲሆን መልካም ጉርብትና የሚል ትርጓሜ እንዳለው ተጠቁሟል።
ድንበር ዘለል ግንኙነቶችን የሚያሳልጡ የተለያዩ የድንበር መተላለፊያዎች ባለፉት አስር አመታት የተዘጉ ቢሆንም ወንጀለኞች እና ስደተኞች በቀላሉ የዘዋወሩ እንደነበር ተጠቁሟል። ባለፈው አመት የሽብር ቡድን የሆነው አልሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ በመግባት ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበር እና በክልሉ የጸጥታ ሀይል እንዲመለስ መደረጉ ይታወሳል።
በኬንያ የብሪታኒያ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ጃኒ ማርዮት በበኩላቸው የቀጠናው ሀገራት ድርቅ፣ የሀብት ግጭት፣ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ እና ሽብር የመሰሉ በርካታ ተግዳሮቶቸ እንዳላቸው አስታውቀው ነገር ግን በርካታ መልካም የሆኑ ነገሮች ያሉት ቀጠና በመሆኑ ፕሮጀክቱ ይህንን ለማጠናከር ይረዳቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ድንበር ዘለል የጸጥታ ስጋቶችን በብቃት ለመቅረፍ የሚያስችል ወቅቱን የጠበቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል። (መረጃውን ከቪኦኤ አገኘነው) አስ