አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4/2015 ዓ.ም፡– የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከሁለት ወር በፊት የአዲስ አበባ ከተማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተደረገውን የወሰን ማካለል ጉዳይ አስመልክቶ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ አዲስ አበባን ለማካለል የተደረገው ስምምነት የኦሮሞን ጥቅም እና ጥያቄን ያላገናዘበ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ መሰረዝ አለበት ሲል አሳሰበ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን ለአዲስስታንዳርድ የሰጡት የኦፌኮ ህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ “ኦፌኮ” በአዲስ አበባ ወሰን ማካለል ጉዳይ ላይ በቅርበት እየተከታተለ መቆቱን እና ለብዙ አመታት ሲታገልበት እንደቆየ አስታውሰው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በወሰነው ዉሳኔ ላይ በጥልቀት ምርምር ላማድረግ ጊዜ እንደወሰደበት ገልፀዋል፡፡ አክለውም “በየትኛውም ሁኔታ ዝም ማለት አንችልም፣ ምርመራ ማድረግ ስላለብን ጊዜ ወስደናል፣ አሁን ተጨባጭ መረጃ ስላገኘንና ሃሳባችንን መግለፅ ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም ለቀጣይ ትግል ማዘጋጀት እቅደናል” ብለዋል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው “የወሰን ማካለል ስራውን ያፀደቁት አካላት አዲስ አበባ ከተማ በወረራ እንደተቋቋመች፣ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ህዝብን ከመሬቱ በስፋት ማፈናቀሏን ከአመኑ በኋላ፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ኦሮሚያ አካባቢዎች 11,000 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው የተስፋፋችው በማለት አሁን ከተማዋ ካለችበት ከ54,000 ሺህ ሄክታር ላይ በመቀነስ 43,000 ሺህ ሄክታር ስፋት እንዳላት እውቅና በመስጠት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ታሪካዊ በደል ፈፅመዋል። የራሳቸውን የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥናት ግኝትን የተቃረነው ይህ የፖለቲካ ውሳኔ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄ የሚመልስ ሳይሆን መደናገርን ለመፍጠር እና ለዓመታት ሲካሄድ የነበረውን የከተማዋን ህገወጥ መስፋፋት እውቅና በመስጠት የህጋዊነት ካባ ለማልበስ የታለመ ነው” ሲል ተቋውሟል።
የኢትዮጰያ መንግስት በነሃሴ ወር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን አዲስ ባጠናው ጥናት መሰረት ማካለሉን ገልፆ ነበር፡፡ የወሰን ማካለሉ ሂደት በአዲስ አበባ ከተማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር ባሉ ሁሉ የካሄደ ሲሆን አንዳድ ቦታዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ሲካተቱ ሌሎቹ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር ተካተዋል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው የከተማዋን ህገወጥ መስፋፋት፣ መስፋፋቱም በኦሮሞ አርሶ አደሮች ላይ ለዘመናት ሲያደርስ የነበረውንና እያደረሰ ያለውን ጉዳት፣ በከተማዋ ላይ የኦሮሞ ህዝብ የሚያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ሊኖር ስለሚገባው መስተጋብር በተመለከተ የባለሙያዎች ኮሚቴ በማቋቋም የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በጉዳዩ ላይ በተለያየ ጊዜ በባለሙያዎች የተካሄዱ ሳይንሳዊ ጥናቶችን፣ አዋጆችን፣ በተለያየ ጊዜ የተዘጋጁ የከተማዋን መሪ እቅዶች፣ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሰት ቻርተር 1991 ዓ.ም፣ የኢፌድሪ ህገመንግሰት፣ የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሰት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተሮች፣ የከተማዋ አርክ ጂአይኤስ ካርታዎችንና መሰል ሰነዶችን እንዲሁም በመሬት ላይ ባለው ተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመስረት የራሱን ጥናት ሲያካሄድ መቆቱን ገልጧል።
በዚህም የምርመራ ግኝት ሀገሪቷን ሲያስተዳድሩ የቆዩ የኢትዮጵያ መንግስታት 100 አመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የኦሮሚያን የገጠር አካባቢዎችን ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንደቀላቀሉና ይህም በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ኑሮአቸውን ያደረጉ አርሶ አደሮችን እንዳፈናቀለ አስረድቷል፡፡
ኦፌኮ ከተማዋን አስመልክቶ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የባለቤትነት ጥያቄ ሆኖ ሳለ፣ ጉዳዩን ወደ ከተማ አስተዳደር ወሰን ጉዳይ አውርዶ መመልከት ተቀባይነት እንደሌለው በመግለፅ እንደ ኦሮሚያ አካል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የአስተዳደር ወሰን ካስፈለገ ህጋዊ እውቅና ያለው ወሰን በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ዘመን እኤአ ከ1991/92 የነበረው በመጠቀም ስፋቱ 22,200 ሄክታር የሚሆን የከተማዋ ቦታ እንዲመለስ እና በሁላቱ አካላት መካከል የተደረገው ስምምነትም ስራ ላይ እንዳይውል እንዲሁም የተፈናቀሉ ሰዎችም ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች ሁሉ በህገመንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት እንዲያስከብር እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አፋን ኦሮሞ እን አማርኛ ጎን ለጎን የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ኦፌኮ ጠይቋል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ አዲስስታንዳርድ በነሃሴ ወር ጥልቅ ትንታኔ ለአንባቢ ማድረሷ ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይም የኦፌኮ ከፍተና አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የወሰን ማካለል ውሳኔ የኦሮሞን ህዝብ እንዲሁም ለረጅም አመታት ንብረታቸው እየተወሰደባቸው ከአዲስ አበባ ሲገፉ ለቆዩት አርሶ አደሮችን ጥያቄ የማይመልስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከሁሉም ጥያቄ በፊት ኦሮሞ በአዲስ አበባ ላይ ያለው የባለቤትነት ጥያቄ መመለስ አለበት ብለው ነበር፡፡አስ