ዜና፡ ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግስት ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያወጣውን መግለጫ እንደማትቀበለው አስታወቀች፤ ግዜውን ያልጠበቀ፣ አባባሽ እና አግላይ ሲል ኮንኗል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12/ 2015 .ም፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በትግራይ ተጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልል የተዛመተውን ጦርነት አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማይቀበለው አስታወቀ። የአሜሪካ ውጭጉዳይ መስሪያ ቤት በጦርነቱ ከፍተኛ ወንጀል ተፈጽሟል ማለቱን እንደማይቀበለው ያስታወቀው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ግዜውን ያልጠበቀ፣ አባባሽ እና አግላይ ሲል ኮንኗል። ሪፖርቱ አንድን ወገን ላይ በማነጣጠር አላግባብ የወነጀለ ነው ሲል ተችቷል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የ2022 አመት በአለም ላይ የታዩ የሰብአዊ መብት ጉዳዮቹን በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ይፋ በተደረገችበት ሪፖርት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የአማራ ሃይሎች በትግራዩ ጦርነት “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” መፈፀማቸውን አስታውቆ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ተጀምሮ ለሁለት አመት በዘለቀው እና ወደ አማራ እና አፋር በተስፋፋው ጦርነት የትግራይ ሀይሎችን ጨምሮ ሁሉም ሀይሎች “የጦር ወንጀል” ፈጽመዋል ብሏል።

ይህንን ሪፖርት በተመለከተ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ እንደማይቀበለው አስታውቆ የአሜሪካን መንግስት ድምዳሜ የተከናነበ ውግዘት ሲል ተችቷል።

አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊ ጥቃት  መሰል ወንጀሎች ተፈጽመው እያለ ግልጽነት በሌለው ምክንያት የአሜሪካን መንግስት መግለጫ አንድን ወገን በተለዩ ወንጀሎች ላይ ተጠያቂ ላለማድረግ ያለመ ነው ሲል ገልጿል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን ለመለየት ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር በተዘጋጀችበት ወቅት ላይ የወጣ በመሆኑም መግለጫው ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ሲል ኮንኗል።

የአሜሪካን መንግስትን ውሳኔ ይፋ ባደረጉበት ወቅት አንቶኒ ብሊንከን ሁለቱን ጎራ ወክለው የሰላም ስምምነቱን የፈጸሙ አካላትም የተፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ያስከተለውን ጉዳት አምነዋል ተቀብለዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ሁሉም አካላት ቃላቸውን በማክበር እምነት የሚያገኝ፣ አካታች እና ሁሉን ያማከለ የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ወንጀል የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲያደርግም አሳስበዋል።  

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአሜሪካ መንግስት መግለጫ ወገንተኛ እና ከፋፋይ  ሲል በመተቸት ይህ የአሜሪካ አካሄድ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ አካታች የሰላም ሂደት እንዲረጋገጥ ስታደርገው የቆየችውን ድጋፍ የሚያጨናግፍ ነው ሲል ገልጿል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.