ዜና፡ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ ካቢኔ ከነባሩ ካቢኔ ጋር የስልጣን ርክክብ አካሄደ

Getachew and Debrestion

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27/ 2015 ዓ.ም – በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከነባሩ አስተዳደር ከዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ስልጣን መረከቡን ይፋ አደረገ። ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ለአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር መልካም ሥራ ተመኝተው፣ የትግራይ ሕዝብ ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ጎን እንደሚቆም ገልፀው ሥራውን እንደምትሠሩት እርግጠኛ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል:: አዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል በጋራ ይሰራል ተብሏል። በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይን ህዝብ ህልውናና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት ሁሉንም የትግራይ ሃብቶች እንደሚጠቀም ተናግሯል።

በአዲሱ ካቢኔ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነዋል። ከተቋቋመ ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የካቢኔ አባላቱን በይፋ ያስተዋወቀው ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 27፤ 2015 በመቐለ ከተማ ባካሄደው ስነስርዓት ነው።

አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረው ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፖለቲካ ፓርቲ የተውጣጡ አባላትን በማካተተት ነው። (ምንጭ፡ ድምጺ ወያነ እና ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.