ዜና፡ በጎረቤት ሱዳን የተፈጠረው ቀውስ ከመቶ በላይ ንጹሃንን መቅጠፉ ተገለጸ፤ በጀነራል አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን መከላከያ ሀይል በአየር የተደገፈ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑ ተጠቁሟል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9/2015 ዓ.ም፡- ከሁለት ቀናት በፊት በሱዳን ካርቱም በሁለቱ ጀነራሎች የሚመራ የሰራዊት ሀይል ግጭት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከመቶ በላይ መድረሱን የሱዳን የዶክተሮች ቡድን መረጃ አመላከተ፤ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውንም አስታውቋል። ጦርነቱ ህይወታቸውነ ከቀጠፈው መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሶስት የዓለም የምግብ ድርጅት ሰራተኞች እንደሚገኝበት የሰብአዊ ረድኤት በድረገጹ አስነብቧል።

በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ውጊያ መካሄድ የጀመረው ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ መሆኑ ይታወሳል።  

የሱዳን መከላከያ ሀይል የልዩ ሀይሉ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ላይ የአየር ሀይል ጭምር በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ አልአረቢያ ጋዜጣ በድረገጹ አስነብቧል። በትላንትናው ዕለት ሁለቱም ሀይሎች ለተወሰኑ ሰአታት ለሰብአዊ ረድኤት ሲባል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርጉም ወዲያውኑ መፍረሱን ዘገባው አመላክቷል።

በካርቱም ኦምድሩማን በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሀገሪቱ መከላከያ ሀይል በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል የጦር ሰፈር ላይ በአየር ላይ የተደገፈ ጥቃት በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ሮይተርስ የአይን እማኞችን በመጥቀስ ዘግቧል።

በአልቡርሃን እና ሃምደቲ በኩል የሚወጡ መረጃዎች እርስ በርሳቸው የተምታቱ መሆናቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመጠቆም ላይ ይገኛሉ፤ ሁለቱም ሀይሎች የሀገሪቱን ቤተመንግስት ጨምሮ የተለያዩ ቦታወችን ተቆጣጥረናል የሚሉ መረጃዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ የጸጥታው ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ሁለቱም ሀይሎች በአፋጣኝ ውጊያውን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። ሀገራቱ ባስተላለፉት መልዕክት እጅግ አስቸጋሪ እና ተለዋዋጭ በሆነው ቀጠናው ላይ የሚታየው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ የሱዳን ጉዳይ ቀጠናውን ይበልጥ እንዳያባብሰው ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአረብኛ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ኢትዮጵያ በሱዳን የተከሰተውን ግጭት በትኩረት እየተከታተለችው እንደምትገኝ ገልጸው ሁለቱም ሀይሎች ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ የተፈጠረውን ግጭት በውይይት እንዲፈቱ እና ግጭቱን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርበዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.