አዲስ አበባ፣ ህዳር 14/ 2015 ዓ.ም፡- በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የክላስተር አደረጃጀትን በመቃወም ለሶስተኛ ጊዜ አርብ እለት የተደረገውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከአንድ መቶ ባለይ የሚሆኑ ወጣቶች መታሰራቸውን የከተማው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ፡፡
የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ሰሚር (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ) እስካሁን ከ 100 በላይ ወጣቶች ተይዘው አይሪሽ አዳራሽ ታስረው እንደነበር የገለፁ ሲሆን አክለውም ከትላንት ወዲያ ወደ 40 የሚጠጉ ወጣቶች ተለቀዋል የሚል መረጃም እንደደረሳቸው አስረድተዋል፡፡
ሰሚር ወጣቶቹ ላይ ድብደባም እደተፈፀመባቸው የገለፁ ሲሆን ትዕዛዝ ተቀብለው ይህንን ተግባር የፈፀሙት ከሌላ አካባቢ የመጡ የፀጥታ ሀይሎ መሆናቸውንም ተናግሯል፡፡
ሌላው ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የወልቂጤ ነዋሪ አርብ እለት በከተማው ስራ የማቆም አድማን ምክንያት በማድረግ የደቡብ ልዩ ሃይሎች በህዝቡ ላይ ድብደባና የስነ ልቦና ጉዳት አያሳደሩበት ነው ብለዋል፡፡
ህዝቡ ሰላማዊ ስራ የማቆም አድማ በማድረግ ላይ እያለ የፀጥታ አካላት ነዋሪውን በመተናኮስ ሁከት እንዲፈጠር አድርገዋል ያሉት ነዋሪው ሆን ተብሎ ህዝቡ ረብሻ ፈጠረ እንዲባል ለማድረግ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ነዋሪው አያይዘውም የፀጥታ አካላቱ አጋጣሚውን በመጠቀም ወጣቶቹን በመደብደብ ለእስር ዳርጓቸዋል በዞኑ የተጣለውን ኮማንድ ፖስቱን በመጠቀም የመብት ጥሰትም እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡
ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ጉራጌ ዞንን ጨምሮ ሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ እና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንዲቀጥሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ በክላስተር የመደራጀት ውሳኔውን በመቃወመም ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ ስራ የማቆም አድማ አድረገው ነበር፡፡
በተጨማሪም የዞን የክላስተር አደረጃጀትን የሚቃወሙ በርካት የዞኑ አመራሮች እና የመምሪያ ኃላፊዎች መታሰራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ህዳር 10 ባወጣው መግለጫ በወልቂጤ ከተማ እየተስተዋለ ያለው ህገ ወጥ ተግባር የዞኑን ማህበረሰብም ሆነ የከተማውን ነዋሪዎች የማይወክልና ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ስብስብ ተግባር መሆኑን ገልፆ የተጀመረውን ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር እንዲተባበር ጥሪ አስተላልፏል ፡፡
አክሎም ይህንን እኩይ ተግባር በመፈፀም ላይ የሚገኘው የህዝባችን የአደረጃጀት ጥያቄን ሽፋን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው በመሬት ዘረፋ የደለበው ፤ በፕሮጀክቶች ጨረታ ብቸኛ አሸናፊ ሆኖ ለዘመናት የከበረው ቡድን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ ሳይሆን ቀይ መስመር ይሆንብኛል ብለው ስጋት ላይ የወደቁት ኮንትሮባንዲስቶች ነፍሳቸው ከስጋቸው ስትለያይ እያሳዩት ያለ ተግባር በመሆኑ የዞኑ መንግስት ህዝቡን ከእነዚህ ሀይሎች ለማዳን ቁርጠኛ አቋም ወስዶ በመስራት ላይ ይገኛል ሲል ገልጧል፡፡
ለህዝብ አጀንዳ ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን በማስላት ህዝብን ለሁከትና ለግጭት እየዳረጉት ያሉትን አካላት ምርመራቸውን በማጣራት በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለማድረግ የተጀመረ ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት አስታውቋል፡፡አስ