ዜና፡ በኢትዮጵያ የአለም የምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች መልቀቃቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29/2015 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ከሳምታት በፊት ማቋረጡን የገለጸው የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስራ ሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ዘኒው ሂዩማኒተርያን የተሰኘ ድረገጽ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አስታወቀ። የአለም የምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለማጣራት ውሳጣዊ ምርመራ ለማካሄድ በሚል እርዳታውን ማቋረጡ ይታወቃል።

የምርምራው ውጤት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ላይ ሃላፊው መልቀቃቸውን የጠቆመው ዘገባው የሃላፊዎቹ መልቀቅ ከተካሄደው የውስጥ ምርመራ ጋር ግንኙነት ይኑረው ወይንም አይኑረው ግልጽ አለመሆኑን አመላክቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በትላንትናው እለት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የሆኑት ማይክ ሃመር ከመሩት ሉዑክ ጋር ባደረጉት ምክክር በእርዳታ እህል አቅርቦቱ መቋረጥ ዙሪያ መወያየታቸውን በማህበራዊ ሚድያ ትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ለማይክ ሀመር እና ሉዑካቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላልተገባ አላማ በስርቆት ውሏል ስለተባለው የእርዳታ እህል በምርመራ ያገኘውን ውጤት እንደገለጹላቸው እና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ጥፋተኞቹን በቅርቡ ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል። የአሜሪካ መንግስት የተቋረጠውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት በአፋጣኝ እንዲያስጀምር መጠየቃቸውንም አካተዋል።

ዘኒው ሂዩማኒተርያን ድረገጽ ባስነበበው ዘገባ የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውዲ ጂቢዳር እና ምክትላቸው ጀኒፈር ቢቶንዲ የተቋሙ ሰራተኞች በተሰበሰቡበት መልቀቂያ ማስገባታቸውን በስብሰባ የታደሙ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።

የድረገጹ ዘገባ እንደሚያመላክተው ከሆነ የተከናወነው የውስጥ ምርመራ ውጤት የሚያሳየው የእርዳታ እህል ከታለመለት አላማ ውጭ የዋለው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ድርቅ ባጠቃቸው አከባቢዎች ሶማሌ ክልል ጨምሮ ተፈጽሟል። በቀጣይ ሳምንታት ሌሎች የተቋሙ ሰራተኞችም ሊለቁ እንደሚችሉ የውስጥ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ድረገጹ በዘገባው አካቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.