አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በትግራይ በ2022 ብቻ በተካሄደው ጦርነት ከ100ሺ በላይ ሰዎች በጦር ሜዳ መሞታቸውን መቀመጫውን ኖርዌ ኦስሎ ያደረገው የሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ያደረገው መረጃ አመላከተ። በአለማችን በ2022 ከተካሄዱ ጦርነቶች ከፍተኛውን ሙት ያስመዘገበው በትግራይ የተካሄደው ጦርነት መሆኑን ያመላከተው ተቋሙ በሁለተኝነት የጠቀሰው በዩክሬን የተካሄደውን ጦርነት ሲሆን ያስከተለው ሞትም ከ81ሺ በላይ መሆኑን አስታውቋል።
በትግራይ በ2022 በተካሄደው ጦርነት ሳቢያ በጦር ሜዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በዩክሬን፣ የመን፣ ማይነማር፣ ናይጀሪያ፣ ሶማሊያ፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ የተካሄዱ ጦርነቶች አንድ ላይ ተደምረው ካስከተሉት የጦር ሜዳ ሞት የላቀ ነው ሲሉ የተቋሙን ጥናት ካካሄዱት መካከል የሆኑት ፕሮፌሰር ሲሪ አስ ሩስታድ ተናግረዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ያካሄደችው ወረራ የአለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረትን የተቆጣጠረ ቢሆንም ከፍተኛ እልቂት ያስተናገደ ጦርነት የተካሄደው ግን በኢትዮጵያ ነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በትግራይ እና በዩክሬን የተካሄዱት ጦርነቶች ሳቢያ በ2022 በአለማችን በጦር ሜዳ የሞቱ ሰዎች ባለፉት 28 አመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሻቅብ ማድረጉን የተቋሙ ጥናት አስታውቋል። በ2022 በአለማችን በተካሄዱ ጦርነቶች ሳቢያ በጦር ሜዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ237ሺ በላይ መሆኑን የኦስሎ የሰላም ጥናት ተቋም ገልጿል። አስ