ከግራ ወደ ቀኝ ሬድዋን ሁሴን፣ ፕሮፌሰር ሞሃመድ ሀሰን፣ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና ጣሃ አብዲ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20/ 2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተወካዮች መካከል እየተደረገ ያለው ንግግር አራተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች በቅድመ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ ውይይቶችን ማድረጋቸውን በጉዳዩ ላይ መረጃ ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
እስካሁን ከተካሄዱት የተለያዩ ንግግሮች መካከል ለሰፋፊ ንግግር መንገድ ለመጥረግ(ለመፍጠር) በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና የተሳትፎ ህጎች ላይ ውይይት ተደርጓል። አንደ ምንጫችን ገለፃ ባለፉት አራት ቀናት የነበረውን ሁኔጻ “የሚበረታታ” መሆኑን ገልፀዋል።
ፍቃድ ስላልተሰጣቸው ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ምንጫችን እስካሁን የተከናወነው ንግግር በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚደረጉ የውይይት ጉዳዮች ላይ እንዳልሆነም ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በፊት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር መሐመድ ሼክ ሂደቱ “በኢትዮጵያ የሚመራ በኢትዮጵያ የሚከናወን” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከኢጋድ በተጨማሪ በኖርዌይና በኬንያ መንግስታት ለንግግሩ ሁኔታዎችን እያመቻቹ ነው ። ነገር ግን አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመላክተው የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ መንግስት በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው፡፡ አዲስ ስታንዳርድን ሃሳባቸውን እነዳካፈሉ ምንጮች ከሆነ እስከ አሁን ድረስ የአውሮፓ ህብረትም ሆነ አሜሪካ በምንም አይነት መልኩ በንግግሩ መሳተፋቸውን የሚያሳይ ምንም አይነት ነገር የለም።
በዚህ በታንዛኒያ ዛንዚባር እየተከናወነ ባለው የድርድር መድረክ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክሎ የሚደራደረውን ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚንስትሩ ዶ.ር ጌዲዮን ጢሞትዎስ፣ የኦሮሚያ ክልል የፍትህ እና ደህንነት ክላስተር በምክትል ሃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ በመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ መረጃ ምክትል ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ደምሰው አመኑ፣ ቦንሳ እውነቱ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በታንዛኒያ የኢትዮጳያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ እንደሚገኙበት አዲስ ስታንዳርድ ማረጋገጥ ችላለች፡፡
በኦሮሞ በፃነት ሰራዊት በኩል ደግሞ ካረጋገጥናቸው ተሳታፊዎች መካከል ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን፣ ጣሃ አብዲ፣ ዶ/ር ባንቲ ኡጁሉ እና ኤጄርሶ ኡርጌሳ ይገኙበታል። አዲስ ስታንዳርድ በሥፍራው ብዙ የኦነሰ ተወካዮች እንደሚገኙ ተረድቷል።