የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ጋሻው አወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2015 ዓ.ም፡– በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የሚመክር ኮንፈረንስ ከነገ ጀምሮ ሊካሄድ ነው ከነገ ሐሙስ ግንቦት 10/2015 ዓ/ም ጀምሮ ሊካሄድ መሆኑን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ጋሻው አወቀ ኮንፈረንሱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ ይካሄዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በኮንፈረንሱ ከ1ሺህ 400 በላይ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የሚሳተፉ ሲሆን ይህንኑ የሚመጥን በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል፡፡
በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ እና የተጀማመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ማሳደግ ዓላማ ያደረገ ኮንፈረንስ መሆኑን በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ትግል ይደረጋል ያሉት ኃላፊው ኮንፈረንሱ የአማራ ክልልን ወደ ፊት ለማስፈንጠር ግብ አስቀምጦ ይመክራል ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱ ለመላው የፓርቲው አመራር እና አባል በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ጋሻው አመራሩ ጠንካራ የፖለቲካ እሳቤና የተስተካከለ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ይጠበቅታልም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡