ዜና፡ በአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ዜጎች የአማራ ብሔር ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ እየታሰሩ ነው ሲል ኢሰመኮ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዛሬ ነሃሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ዜጎች በአማራነታቸው ብቻ እየታሰሩ ነው ሲል ገልጿል። በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ንጹሃን ዜጎች በግጭቱ ሳቢያ ሂወታቸው ማለፉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለው መሆኑን ጠቁሞ አዲስ አበባን ጨምሮ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከመተላለፉት በፊት እና በኋላ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች እንደደረሱት አመላክቷል።

በአዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ እስር እየተፈጸመ ነው ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ በተጨማሪም በከተማዋ የሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የዘፈቀደ እስር እየተፈጸመ ነው ብሏል። ኮሚሽኑ የእስረኞች አያያዝን ለመከታተል እድልቻለም አስታውቋል።

ከባድ መሳሪያ የተደገፈ ፍልሚያ በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በመንግስት እና በታጣቂ ሃይሎች መካከል መካሄዱን ማረጋገጡን ያስታወቀው ኮሚሽኑ መንገድ ለመዝጋት ሲሞክሩ የነበሩ ነዋሪዎችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን አመላክቷል።

ታጣቂ ሀይሎች በክልሉ በየደረጃው በሃላፊነት የተመደቡ ሰዎችን ዋነኛ ኢላማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የክልሉ የመንግስት መዋቅር በጊዜያዊነት እንዲፈርስ ማድረጉን እና ሃላፊዎችም መገደላቸውን አስታውቋል።

በደብረብርሃን፣ ፍኖተሰላም፣ ቡሬ ከተሞች በከባድ መሳሪያ በተደረገፈ ጥቃት በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን፣ መኖሪያ ቤቶች እና የህዝብ መገልገያዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ታማኝ ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል።

በደብረብርሃን ከተማ በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት አከባቡ በከባድ መሳሪያ ፍንጣሪ እና በተኩስ ልውውጥ ነዋሪዎች መገደላቸውን ጠቁሟል። በባህርዳር ንጹሃን ነዋሪዎች በጎዳና ላይ ወይንም በቤቶቻቸው ግድያ ተፈጽሞባቸዋል ሲል መግለጫው አካቷል። በጎንደር እና ሽዋሮቢትም ተመሳሳይ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚያመላክት ሪፖርት እንደደረሰው አመላክቷል። ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ እና ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል።

ተፋላሚ ሀይሎች ሁሉንም ጥቃቶች እንዲያቆሙ፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ ለውይይት እና ለሰላማዊ መፍትሔዎች በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ኮሚሽን በመግለጫው ጠይቋል። የፌደራል መንግስቱ የዘፈቀደ እስር ከማድረግ እንዲቆጠብ፣ ማጎሪያ ቦታዎችን እና እስር ቤቶችን በሚመለከታቸው አካላት እንዲጎበኙ እንዲፈቅድ፣ በእስር ላይ የሚገኙትንም እንዲፈታ አሳስቧል።

ታዋቂ ሰዎች፣ መሪዎች እና የመንግስተ ባለስለጣናት ሁኔታውን ከሚያባብስ ንግግር እንዲቆጠቡም ጥሪ አቅርቧል። የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ የተለያዩ ተቋማት ተፋላሚ ሀይሎች ወደ ጠረንጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.