አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28/ 2015 ዓ.ም፡- ከመጪው 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ የሀገሪቱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ የማያደርጉ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች (international school) የሚማሩ ተማሪዎች የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል መልቀቂያን ጨምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና መፈተን እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ የ2015 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ባደረጉበት መድረክ እንደገለፁት አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተብለው የተቀመጡ ትምህርት ቤቶች የአገሪቷን ስርዓተ ትምህርት ሳይሆን የሌላ አገር ስርዓተ ትምህርትን የሚተገብሩ በመሆኑ ተማሪዎች የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ጨምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተናን አይወስዱም ብለዋል፡፡ ወላጆች ከወዲሁ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ እንዲወስኑም አስገንዝበዋል፡፡
የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ትምህርት ቤቶቹ የአገሪቱን ስርዓተ ትምህርት በመጥላትና አስፈላጊ አይደለም በማለት ተማሪዎችን በራሳቸው መንገድ ይዘው እንደሚሄዱ ገልፀው የተማሪዎቹን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለወላጆች ትተናል ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በርካታ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች አግባብ ባልሆነና ህግና መመሪያን በልጠበቀ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት ኃላፊው ትምህርት ቤቶቹ የአገሪቱን ስርዓተ ትምህርት መቀበል ካለመፈለግ በተጨማሪ ከቁጥጥር ለመውጣት በተለይም ወላጅ ላይ አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እንዲመቻቸው በማንአለብኝነት በመንቀሳቀስ ራሳቸውን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ብለው እንደሚጠሩ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ስርዓተ ትምህርት በመጥላትና በመሸሽ የሌላ አገርን ተግባራዊ የሚያደርጉ ትምህርት ቤቶች የአገሪቱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እንዲያደርጉም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡
ከሶስት አስርት አመታት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ከተማ አቀፉ የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 73,667 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደው 80.2% ያህሉ 50 ፐርሰንት እና ከዛ በላይ በማምጣት ማለፋቸውን ትምህርት ቢሮው አስታውቋል፡፡ 67,939 ከሚሆኑ የቀን ተማሪዎች መካከል 56,842 የሚሆኑት ማለትም 83.6 % ያህሉ የማለፊያ ውጤቱን በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን መዘዋወራቸውን ቢሮው ሓምሌ 25 ቀን ባወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡አስ