ዜና፡ በታንዛኒያ ሲደረግ በቆየው ውይይት ስምምነት ላይ አለመድረሱን ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት አስታወቁ

ከግራ ወደ ቀኝ ሬድዋን ሁሴን፣ ፕሮፌሰር ሞሃመድ ሀሰን፣ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና ጣሃ አብዲ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 ዓ.ም፡- በመንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ ሲካሄድ በቆየው የሰላም ውይይት፣ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በየግል ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ ሲሆን ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡

ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል ብሏል መግለጫው።

ችግሮችን በውይይት የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ፅኑ አቋም አለው ያለው መግለጫው የሰላም ውይይቱን ላመቻቹና ላስተናገዱ አካላት የኢፌዴሪ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ ባወጣው ምግለጫ የመጀመሪያው የድርድሩ ምዕራፍ ዛሬ መጠናቀቁን ገልፆ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጧል፡፡

ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በቀጣይ ተገኛኝተው ውይይቱን በማስቀጠል በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ግጭትን ለመፍታት መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡ አክሎም አሁንም ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጧል፡፡ በመጨረሻም ውይይቱ እነዲካሄድ ላመጫቹ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በታንዛኒያ ዛንዚባር ሲከናወን የቆየውን የድርድር መድረክ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚንስትሩ ዶ.ር ጌዲዮን ጢሞትዎስ፣  የኦሮሚያ ክልል የፍትህ እና ደህንነት ክላስተር በምክትል ሃላፊ ከፍያለው ተፈራ፣ በመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ መረጃ ምክትል ሀላፊ ሜጀር ጀነራል ደምሰው አመኑ፣ ቦንሳ እውነቱ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በታንዛኒያ የኢትዮጳያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ መወከላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግባለች፡፡

በኦሮሞ በፃነት ሰራዊት በኩል ደግሞ ካረጋገጥናቸው ተሳታፊዎች መካከል ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን፣ ጣሃ አብዲ፣ ዶ/ር ባንቲ ኡጁሉ እና ኤጄርሶ ኡርጌሳ ከተሳታፊዎች መካከል መሆናቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.