ዜና፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በተፈጠረው ግጭት ፖሊስ ህፃናት ተማሪዎችን ማሰሩን ኢሰመኮ አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ለአካለ መጠን ያለልደረሱ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አወገዘ። 

የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር በመደረጉ ከታህሳስ ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፀጥታ መደፍረሰ ተሰተውሏል፡፡

ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል ያላቸውን 72 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል

ኮሚሽኑ ትላንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የፖሊስ አባላት የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠር በወሰደው የእስር እርምጃ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈፅመዋል፡፡ 

አሰመኮ “በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ የተማሪዎችና የትምህርት ቤቶች ንብረት ወድሟል፣ እንዲሁም ሕፃናት ተማሪዎች ለአካላዊ እንግልት እና ከሕግ አግባብ ውጭ ለእስር ተዳርገዋል” ያለ ሲሆን  አክሎም በአንዳንድ ሚዲያ በግጭቱ የአንድ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል የተባለው መረጃ ትክክለኛ አለመሆኑን አረጋግጫለው ብሏል፡፡

እንደ መግለጫው ዕድሜያቸው በአብዛኛው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ተማሪዎች ከመነሻው ለእስር መዳረጋቸው እና ለተለያየ ጊዜ መጠን በእስር መቆየታቸው ተገቢ ያልሆነና ለሁኔታውም ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ነው፡፡ 

የበርካታ ሕፃናት ተማሪዎች እስር የተሟላ አገልግሎት በሌላቸውና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች መሆኑ የአስፈላጊነት፣ የሕጋዊነትና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕፃናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር መሆኑን መግለጫው ገልጧል፡፡ 

ኢሰመኮ ለተማሪዎች መታሰር ምክንያት  የሆነው የጸጥታ መደፍረስ መነሻው  በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የክልሉ መዝሙር እንዲዘመር በመደረጉ የተለያየ ሃሳብና ፍላጎት ባላቸው ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት መሆኑን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ የሌላ ክልልን ባንዲራ በአስገዳጅነት መስቀል ህጋዊ መሰረት የሌለው እና አላስፈላጊ ውዝግቦችን የሚፈጥር እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት መሆኑን ገልጿል።

መንግሥት ውሳኔዎች፣ ደንቦች፣ ፕሮግራሞች፣ መርኃ ግብሮች ወይም አሠራሮች ሲዘጋጅ ከመተግበራቸው በፊት በሰብአዊ መብቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤቶች አስቀድሞ መለየት፣ ማጤንና መከላከል ወይም መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል ሲል አሳስቧል ኮሚሽኑ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.