ዜና፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ በሶስት ሊቀጳጳሳት እና 25 ተሿሚ ጳጳሳት ላይ የውግዘት ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከቀኖና እና ከእውቅናዬ ውጭ የሆነ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት እና ጳጳሳት ሹመት ተስጥቷል በተባለው ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባካሄደው አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ፣ ሲመቱን በሰጡ ሊቀጳጳሳት እና ተሿሚዎች ላይ የውግዘት ውሳኔ አሳለፈ።  

የውግዘት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሶስቱ ሊቀጳጳሳት ብጹእ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹእ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብጹእ አቡነ ዜና ማርቆስ ናቸው።

በኦሮምያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በሶዶ ዳጬ ወረዳ በወሊሶ ከተማ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀኖና ውጭ ተፈጽሟል የተባለውን የ26 ጳጳሳት ሹመት ከሰጡት ብጹዕ በአቡነ ሳዊሮስ በተጨማሪም፣ ሲኖዶሱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከተሿሚዎቹ መካከል 25ቱ መነኮሳትም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ጉባኤ ተለይተው እንዲወገዙ ተወስኗል።

ከተሿሚዎቹ መካከል አባ ፀጋዘአብ አዱኛ የተባሉ አባት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ይቅርታ በመጠየቃቸው ውሳኔው እንደማይመለከታቸው ተጠቁሟል።

ሲኖዶሱ በጋዜጣዊ መግለጫው ካካተታቸው ውግዘቶችም መካከል ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለውን ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻርና ማዕረጋቸውን በማንሳት እንደለያቸውና ከጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው  “አቶ”  እየተባሉ እንዲጠሩ መወሰኑን አሳውቋል።

በቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተክርስቲያን እንደለያቸው አጽንኦት ሰጥቶ ይፋ አድርጓል። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ የለያቸው አባቶች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከቶች ሌሎች ብፁዐን አባቶች እንዲመደቡም ወስኗል፡፡

ሲኖዶሱ በተጨማሪም በመግለጫው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት አብያተ ክርስትያናት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ _ ፓትርያርክ ውጭ የሚደረግ ሢመትን እንደማይቀበሉና ዕውቅና እንደማይሰጡ በላኩት የአቋም መግለጫ አሳውቀውኛል ብሏል። ለዚህም ምስጋናውን አቅርቧል።

በሌላ በኩል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሳዊሮስ በዓለ ሲመቱ ከተከናወነ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሲመቱን ለመፈጸም ያበቋቸውን አስገዳጅ ሁኔታዎች መዘርዘራቸው ይታወሳል። ከተዘረዘሩት ምክንያቶችም መካከል በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸው ዘንድ አከባቢያቸውን የሚያውቁ እንዲሁም ቋቋቸውን የሚናገሩ አገልጋዮች ሊኖራት እንደሚገባ አመላክተው ይህ ባለመደረጉ ቤተክርትሲያኗ በተለይም በኦሮምያ እና ደቡብ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞቿን አጥታለች የሚለው ይገኝበታል።

አቡነ ሳዊሮስ አክለውም 85በመቶ የሚሆነው የሲኖዶሱ አባላት ከአንድ አከባቢ የመጡ መሆናቸውን በመጥቀስ የቤተክርስቲያኗን የብሔር ስብጥር የማያንጸባርቅ ሲሉ መተቸታቸው ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.