ዜና፡ ሲፒጄን ጨምሮ 47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም ሲሉ ለጠ/ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24/2015 ዓ.ም፡- የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄን ጨምሮ 47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም ሲሉ ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ። የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ያልተገደበ የኢንተርኔት እና የዲጂታል ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የማግኘት መብትን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል።

መንግስት ኢንተርኔትን በመዝጋት እንደመሳሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል ሲሉ ስጋታቸውን በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት ድርጅቶቹ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በሀገሪቱ አገልግሎቶቹ የተቋረጡበትን ሁኔታ በማሳያነት አቅርበዋል።

ኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት መሰረታዊ የሰብአዊ መብትን መጋፋት እና የጋዜጠኞችን መብት እና ደህንነትን ማሳጣት ነው ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው ሞግተዋል።

ድርጅቶቹ ለጠ/ሚኒስትሩ የጻፉትን ደብዳቤ በግልባጭ ለሳፋሪኮም የቴሌኮም ኩባንያ፣ ለኢትዮቴሌኮም እና ሌሎች ስድስት ባለድርሻ ተቋማት ልከዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.